ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ባህር ዳር ከተማ

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወደ ሜዳ የሚመለስበትን የመጀመሪያ ጨዋታ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

11ኛው ሳምንት ላይ አራፊ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ከ18 ቀናት በኋላ ወደ ሜዳ ይመለሳሉ። ከደካማው አካሄዳቸው አገግመው ከወራጅ ቀጠናው ቀና ካሉባቸው ሁለት ድሎች በኋላም ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ለመጠጋት ባህር ዳርን ይገጥማሉ።

ውድድሩ ዕረፍት ላይ በሰነበተባቸው ቀናት ስብስባቸው ላይ ሰፋ ያለ ለውጥ ያደረጉት ድቻዎች 11 የሚደርሱ ተጫዋቾቻቸውን አሰናብተው ሁለት የውጪ ዜጎችን ጨምሮ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ደግሞ አስፈርመዋል። ይሁን እንጂ ቡድኑ እስከ ውድድሩ አጋማሽ አዳዲስ ፈራሚዎቹን የማይጠቀም መሆኑ በነገው እና በቀጣዩ ጨዋታ አማራጮቹን እንዳያጠብበት ያሰጋል። በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ ጥሩ አቋም ያሳየው ነጋሽ ታደሰ እና ያሬድ ዳርዛ ዓይነት ተጫዋቾች መቀነስ ቡድኑ ያልታሰቡ ጉዳቶች ከገጠሙት እንዳያጎሉት ያሰጋዋል። በአቀራረብ ደረጃ ግን ድቻ ጅማ ላይ ወደ ውጤት በተመለሰበት አኳኋን ጥንቃቄ አዘል አቀራረብ ላይ ትኩረት አድርጎ በፍጥነት በተጋጣሚው ሜዳ ለመገኘት ጥረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ይህንን ሂደት ሲያቀላጥፍ የሚታየው ፀጋዬ ብርሀኑም በግሉ ጭምር በተጋጣሚ ተከላካዮች ላይ የሚፈጥረው ጫና ለድቻ የግብ ዕድሎችን ሲያመጣ መመልከታችን ደከም እያለ ለመጣው የባህር ዳር የኋላ ክፍል ምን ያህል ፈተና ሊሆን ይችላል የሚለውን እንድንጠብቅ የሚያደርግ ነው።

ወላይታ ድቻ ዋነኛ አጥቂው ስንታየሁ መንግሥቱ አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኝ ሲሆን አማካዩ ኤልያስ አህመድም በቤተሰብ ጉዳይ ምክንያት ከቡድኑ ጋር እንደማይገኝ ሰምተናል።

ውድድሩ ወደ ከተማው የመጣለት ባህር ዳር ከተማ በጅማ ቆይታው ወደ ላይኛው ፉክክር ራሱን መቀላቀል የሚችልባቸውን ዕድሎች አምክኖ ተመልሷል። የነገው ጨዋታም ቡድኑ ከሦስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ጥረት የሚያደርግበት ይሆናል።

ባህር ዳር በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ላይ የመከላከሉ ረገድ ይታየበት ድክመት ነገም ውጤት ይዞ ለመውጣት የሚፈተንበት ጉዳይ ነው። የተረጋጋ የኋላ ክፍል የተጫዋቾች ምርጫ የነበረው ቡድኑ በተለይ በጅማው ጨዋታ በራሱ ሳጥን ውስጥ የታየበትን ድክመት በተመለከተ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ገልፀው የነበሩት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በዕረፍቱ ቀናት ይህንን ችግር ለመቅረፍ ጥረት እንዳደረጉ ይታመናል። ያም ቢሆን ከአሰላለፍ ምርጫ አንፃር ቡድኑ ለውጦች ሊያደርግ የሚችልበት ዕድል ይኖራል። ተጋጣሚው በፍጥነት ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመድረስ ረገድ ካለው ጥንካሬ አንፃር ሲታይም ይህ ጉዳይ ትኩረት ቢስብ አይገርምም። ከዚህ ውጪ የምንይሉ ወንድሙ መልካም አቋም ላይ መገኘት ከባዬ ገዛኸኝ ከጉዳት ማገገም እና ጨዋታዎች መሳተፍ አንፃር ፊት መስመር ላይ ቡድኑ ጥሩ አማራጭ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው። ነገር ግን ባህር ዳር ከተከላካይ መስመር ጀርባ ክፍት ቦታ ሲያገኝ አሰፈሪነቱ የሚታይበትን ሁነት ከድቻ ጥንቃቄ አዘል እና ለግብ ክልሉ ቀርቦ ከሚከላከልበት አቀራረብ አንፃር በቀላሉ ላንመለከተው እንችላለን።

በባህር ዳር ከተማ በኩል አቤል ውዱ አሁንም ከጉዳት ያልተመለሰ ሲሆን ከጉዳቱ አገግሞ ልምምድ የጀመረው ሳምሶን ጥላሁንም ለነገው ጨዋታ እንደማይደርስ ሰምተናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በ2011 የውድድር ዓመት በሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱንም በተመሳሳይ በ1-1 ውጤት ተለያይተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (3-5-2)

መክብብ ደገፉ

መልካሙ ቦጋለ – አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ

አናጋው ባደግ – መሳይ ኒኮል – በረከት ወልዴ – እንድሪስ ሰዒድ – ያሬድ ዳዊት

ፀጋዬ ብርሀኑ – ቢኒያም ፍቅሬ

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ጽዮን መርዕድ

ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – አፈወርቅ ኃይሉ

ሳላምላክ ተገኝ – ፍፁም ዓለሙ – ግርማ ዲሳሳ

ምንይሉ ወንድሙ