ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የሳምንቱን ዐበይት ጉዳዮችን የምናገባድደው እንደተለመደው ሌሎች የትኩረት ነጥቦችን በማንሳት ነው።

👉አስደናቂው የባህርዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም መጫወቻ ሜዳ

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ከ12ኛ ሳምንት አንስቶ የማስተናገድ ተራውን የወሰደው የባህርዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም እስካሁን ውድድሩ ከተካሄደባቸው ብሎም በሀገሪቱ ከሚገኙ ስታድየሞች የምቹው የመጫወቻ ሳር ባለቤቱ ነው ቢባል ለስህተት የሚዳርግ አይመስልም።

አረንጓዴማ መልኩ በጨዋታዎች የቀጥታ ስርጭት ወቅት ለውድድሩ ከሚሰጠው ውበት ባልተናነሳ በአስገራሚ እንክብካቤ እና ጥንቃቄ እንደተያዘ የሚመሰክረው ሜዳው ኳስን መቆጣጠር ለሚሹ ቡድኖች እጅግ ምቹ መደላድልን ሲፈጥር ተመልክተናል። ከዚህ በተጨማሪ በጨዋታዎች ወቅት የሚጎዱ ቦታዎችን መልሶ ለማስተካከል በቶሎ የሚወሰድው እርምጃ ይበል የሚያሰኝ ነው። በሜዳው መልካም ገፅታ ሳይዘናጉ ይህ በጎ መልኩ እንዲቀጥል ከስር ከስር የሚከወኑ ሥራዎች ያላቸው አስተዋፅዖ ከፍ ያለ መሆኑንም አፅዕኖት ለመስጠት እንወዳለን። ከዚህ ባለፈ በጉድለት የሚነሳው ሜዳው ላይ ያሉት መስመሮች የመፍዘዝ ጉዳይ ነው። በተለይም ጨዋታውን በቀጥታ ስርጭት የሚያስተላልፉ ኮሜንታተሮች በጉዳዩ ላይ ቅሬታ ሲያቀርቡ መሰማታቸው በጨዋታ ቀናት ቡድኖች ከመድረሳቸው አስቀድሞ ንጋት ላይ መስመሮችን የማድመቅ ሥራ አሁን ካለው በላይ ትኩረት እንዲሰጠው የሚጠቁም ሆኖ አግኝተነዋል።

👉 ከባህርዳር እና ድቻ ጨዋታ በፊት የሆነው ምንድነው ?

የባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም በዘንድሮው የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ ከሆነው የባህር ዳር ከተማ እና ወላይታ ድቻ በፊት የተፈጠረው ክስተት ትኩረትን የሚስብ ነበር።

ተጋጣሚ ቡድኖች ዘግይተው መምጣት ይሁን በቅድመ ዝግጅት መጓደል ባይታወቅም የሁለቱ ቡድን ተጫዋቾች ለማሟሟቅ ወደ ሜዳ ከገቡ ወዲህ ከተፈቀደው ደቂቃ ያነሰ መጠን አሟሙቀው እንዲገቡ የተደረጉ ሲሆን በጥድፊያ ወደ መልበሻ ክፍል ካመሩ በኃላም ወደ ሜዳ ለጨዋታው ለመግባት ተዘጋጅተው በመግቢያው ኮሪደር ላይ በነበሩበት ወቅት የሱፐር ስፖርት የቅድመ ጨዋታ ትንታኔ አለመጠናቀቁን ተከትሎ ተጫዋቾቹ ለ7 ያህል ደቂቃዎች በኮሪደር ላይ እንዲቆዩ ተገደዋል። በዚህም ቅር የተሰኙት የባህር ዳሩ ዋና አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ሁኔታው የፈጠረባቸውን ቅሬታ ለውድድሩ አስተባባሪዎች ሲያቀርቡ ተመልክተናል።

👉 የተሻሻለው የኢትዮጵያ ቡና መለያ

ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር የአጋርነት ስምምነት ከፈፀመ ወዲህ ቡድኑ በጅማው ውድድር ላይ ይጠቀምበት የነበረው መለያ ላይ የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ አርማ የታተመበት የመለያው ቦታ ከዕይታ አንፃር ጥያቄዎች እየተነሱበት መቆየቱ ይታወሳል። ታድያ ሊጉ ከሁለት ሳምንት ዕረፍት ሲመለስ ኢትዮጵያ ቡናዎች በመለያቸው ላይ ማሻሻያዎችን አድርገው ቀርበዋል።

በዚህም የባንኩ አርማ ለዕይታ የታሸለ በሚባለው የመለያው የቀኝ እጀታ ላይ እንዲሆን ተደርጓል ፤ በተጨማሪም በመለያው በስተጀርባ የነበረው በደቃቁ ይፃፍ የነበረው የተጫዋቾቹ ስምም መጠኑ ከፍ እንዲል ተደርጓል።

👉 የኮቪድ ተፅዕኖ የበረታበት የጨዋታ ሳምንት

ለዓምናው ውድድር መቋረጥ ለዘንድሮውም አካሄድ መቀየር ምክንያት የሆነው የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ተፅዕኖ በዚህ ሳምንት በርትቶ ታይቷል። እንደሚታወቀው የተሳታፊ ቡድኖች አባላት የቫይረሱ ምርመራ እየተደረገላቸው የተገኘባቸው ከስብስቡ እየተለዩ ጨዋታዎች ሲከወኑ እንደነበር የሚታወቅ ነው። ሆኖም ከጅማው ውድድር መጠናቀቅ በኋላ በነበረው የዕረፍት ጊዜ ተጨዋቾች ራሳቸውን ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት ጥያቄ ውስጥ በሚከት አኳኋን ከሌላው ጊዜ በተለየ በርከት ያሉ ተጨዋቾች ምርመራውን ማለፍ ሳይችሉ ከጨዋታ ውጪ ሆነው መታዘብ ችለናል።

ችግሩ ያገኛቸውን ተጨዋቾች ስም መጥቀሱ የሚደገፍ ባይሆንም ከአንድ ቡድን ሰባት የሚደርሱ ተጫዋቾች የተጠቁበትን ሁኔታ ጭምር ታዝበናል። የቡድን አባላት ውሎ እና አዳራቸው ተመሳሳይ ከመሆኑ አንፃርም የሚያደርጉት ጥንቃቄ ከራሳቸው አልፎ ለጓደኞቻቸውም ጭምር ከመሆኑ በተጨማሪ በቡድናቸው ውጤት ላይም ከፍ ያለ ተፅዕኖ ስለሚኖረው ጉዳዩ የሚመለከታቸው የየቡድኑ አባላት ሁሉ ከሌላው ህብረተሰብ ጋር በሚኖራቸው ቅርርብ ተገቡውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰብ እንወዳለን።

👉 በቀድሞው ክለቡ የታከመው ቴዎድሮስ ገብረእግዚአብሄር

በቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድኖች ውስጥ አልፎ ዓምና እየተመላለሰ ለዋናው ቡድን ሲጫወት የነበረው አማካዩ ቴዎድሮስ ገብረእግዚያብሔር ዘንድሮ ወደ አዳማ ከተማ መጥቷል። ታድያ ሰሞንኛ አቋሙ መልካም ሆኖ በመገኘቱ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ደጋግሞ መግባት የቻለው ተጫዋቹ በዚህ ሳምንትም የቀድሞው ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በገጠመው ስብስብ ውስጥ መካተት ችሏል። ከእንቅስቃሴው ውጪ ትኩረት ይስብ የነበረው ጉዳይም የታየው ተጫዋቹ 37ኛው ደቂቃ ላይ በትከሻው ላይ ጉዳት ሲያስተናግድ ነበር። ሁኔታው እንደሚታወሰው አዳማ ከተማ 10ኛው ሳምንት ላይ የህክምና ባለሙያውን በቀይ ካርድ በማጣቱ ቴዎድሮስ በቀድሞው ቡድኑ ባለሙያዎች ህክምና እንዲደረግለት ያስገደደ ሆኖ አልፏል።

👉 አሁንም ሙሉ መሆን ያልቻለው የጨዋታ በፊት ዝግጁነት

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንዳነሳነው ከሱፐር ስፖርት ወደ እግርኳሳችን መምጣት ጋር በተያያዘ አስፈላጊነቱ ይበልጥ የጨመረው ከጨዋታ ሳምንታት መጀመር በፊት እና ከአንድ ነጠላ ጨዋታ ቀደም ብሎ የሚከወኑ ሥራዎች አሁንም ጉድለት አላጣቸውም። ከላይ በወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ጨዋታ መጀመር አስቀድሞ ስለነበረው ውዥምብር ካነሳነው ሀሳብ ውጪ የነበሩ ሌሎች ጉድለቶችን አንድ ላይ ለማንሳት ወደናል።

ቀዳሚው በአዲስ አበባ እና በጅማ በእጅጉ ተስተካክሎ ያየነው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የመግቢያ በር ላይ መዋከብ ጉዳይ ነው። የውድድር ቦታዎች በተቀየሩ ቁጥር ለጉዳዩ አዲስ ለሆኑት ፀጥታ አካላት ተገቢውን መረጃ በማስተላለፍ ንትርኮች ከመፈጠራቸው አስቀድሞ መፍትሄ ማበጀት የአውዳዳሪው አካል ግዴታ ነው። ሆኖም ለውድድሩ ሽፋን የሚሰጡ ሚዲያዎች በቁጥር ሲመናመኑ ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት አብሮ መውረድ ብዙ ዋጋ ከፍለው በቦታው የሚገኙ ሚዲያዎችን ሞራል የሚነካ ሆኗል። ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ማስተካከያ ለማድረግ በሚመለከታቸው አካላት ጥሩ መነሳሳት ቢታይም የጨዋታ ቀናት ተቀይረው ዘብ የሚቆሙ የፀጥታ አካላት ሲለወጡ በድጋሚ በጭቅጭቅ ውስጥ ማለፍ ለሚዲያ አካላት የጊዜ ብክነት መሆኑ እንዲቆም አሁንም ጉሳዩ የተሟላ ትኩረት ያገኝ ዘንድ አበክረን እንጠይቃለን። ይህ ጉዳይ በሚዲያ ብቻ ሳይሆን በኳስ አቀባዮች ላይም ተከስቶ ሥራውን የሚከውኑ ታዳጊዎች ‘ባጃችሁ ፎቶ የለውም’ በሚል በር ላይ ሲንገላቱ ተመልክተናል።

ሌላው የቡድኖች አሰላለፍ ዝርዝር ጉዳይ ነው። ከዚህ ቀደም እጅግ አሰልቺ በሆነ እና ቸልተኝነት በሚያጠቃው መንገድ የቡድኖችን አሰላለፍ ጨዋታዎች ጥቂት ደቂቃዎች እስኪከሩት ድረስ ማግኘት ያስቸግር ነበር። ምስጋና ለሱፐር ስፖርት መምጣት ይግባና ዘንድሮ የቡድኖች አሰላለፍ በተሻለ ጥራት ተዘጋጅተው ለሚዲያ ግብዓት ሲውሉ ቆይተዋል። በባህር ዳሩ ውድድር የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ግን እዚህ ላይም ጉድለት አስተውለናል። የመጨረሻው የቡድኖች ስብስብ መግለጫ በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ስህተቶች ኖረውበት ያየን ሲሆን ስህተቱ ከራሳቸው ከቡድኖቹ የመጣ መሆኑ ቢገለፅም ባደረግነው ማጣራት የቡድኖቹ አሰልጣኞች ትክክለኛውን ስብስብ ስለማሳወቃቸው ተናግረዋል። ኃላፊነቱን የሚወስደው ማንም ይሁን ማን ግን ስህተቶችን ለማስተካከል የሚወስደው ጊዜ መርዘም የሚዲያዎችን ሥራ ማስተጓጎሉ አልቀረም።

ከዝግጅት አንፃር የታዘብነው ሌላው ጉዳይ የቀይ መስቀል ሰራተኞች መቀመጫ ጉዳይ ነው። ጅማ ላይ የፀሀይ መከለያ ዳስ ተጥሎላቸው እና መቀመጫ ተዘጋጅቶላቸው ከፀሀይ ተከልለው በንቃት የተጎዳ ተጫዋችን ለማገዝ የሚሰማሩት ባለሙያዎቹ ባህር ዳር ላይ ችላ የተባሉ ይመስላል። ውድድሩ ሲጀምር የቀይ መስቀል አባላቱ ያላዳስ እና መቀመጫ ሜዳ ላይ በፀሀይ ቁጭ ብለው መመልከታችንም ለዚህ ሀሳባችን መነሻ ሆኖናል። እርግጥ ነው ሁለተኛው ቀን ላይ አባላቱ ዳስ አዘጋጅተው ችግሩን ለመረፍ ያደረጉትን ጥረት ተመልክተናል። ሆኖም ከሜዳው ስፋት አንፃር ዳሱ ራቅ ብሎ መጣሉ ጉዳት የደረሰበትን ተጫዋች ከሜዳ ለማውጣት የሚፈጀው ጊዜ በፋሲል እና ሀዋሳ ጨዋታ ላይ በተመደቡት የጨዋታ ኮሚሽነር ቅሬታ እንዲነሳበት አድርጓል።

በጥቅሉ ውድድሩን ለሁሉም አካላት ምቹ ለማድረግ በርካታ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ ማስገባት እና ሁሌም ተመሳሳይ ትኩረት በመስጠት መስራት በእጅጉ አስፈላጊ ስለመሆኑ መጠቆም እንወዳለን።

👉 የተዘነጋው የኮቪድ ፕሮቶኮል

አዲስ አበባ ላይ በነበረው ውድድር በነበሩ ክፍተቶች ሳቢያ ለውድድሩ አረንጓዴ መብራት የሰጠውን የጤና ጥበቃ ሚኒስትርን ትኩረት ጭምር ስቦ የነበረው ቸልተኝነት ባህር ዳር ላይም ተመልክተነዋል። በመዲናዋ በድምፅ ማጉያዎች በተደጋጋሚ ይለፈፍ የነበረው የኮቪድ ፕሮቶኮል እና የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ጉዳይ በባህር ዳር የተዘነጉ መስለዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከአፍ መሸፈኛ ጭምብሎች አጠቃቀም አስገዳጅነት ዙሪያ መዘንጋት ከመታየቱ በላይ በስታድየም የሚገኙ ግለሰቦች ቁጥር በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ ከፍ ብሎ መገኘት መነሳት የሚገባው ነጥብ ነው። በደጋፊ ማኅበራት በኩል ቡድናቸውን በውስን ቁጥር እንዲደግፉ ብቻ ፍቃድ የተሰጣቸው የተወሰኑ ክለቦች ደጋፊዎች ቁጥር እንደታዘብነው ከሆነ አንዳንዴ ከ40 በላይ ሲደርስ ተመልክተናል። ይህ ጉዳይ ከቫይረሱ ስጋት በተጨማሪ በክለቦች መሐል አድልኦ እየተፈጠረ ነው የሚል ቅሬታ የሚያስነሳ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የክለባቸውን መለያ ከለበሱ ደጋፊዎች በተጨማሪም በተለያዩ ኃላፊነቶች ወደ ስታድየም የሚገቡ ታዳሚዎች ቁጥር ከፍ ማለት እና በመሀላቸው ያለው ርቀት ያለመጠበቁ ጉዳይም በቀጣይ የጨዋታ ሳምንታት ሊታረም ይገባል።

👉 ወደ ግብግብ ሊያመራ የነበረው አለመግባባት

የእግርኳስ ውድድሮች ክንውን የበርካታ አካላት እና ግለሰቦችን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ይታወቃል። ይህ በመሆኑም አልፎ አልፎ አለመግባባቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ዕሙን ነው። በዚህ ሳምንትም በመጨረሻው ጨዋታ መጀመሪያ አካባቢ የፋሲል ከነማ ቡድን አሟሙቆ ወደ መልበሻ ክፍል ባመራበት ወቅት በክለቡ እና በአወዳዳሪው አካል የመጫወቻ ኳሶች መደበላለቅ መነሻነት አለመግባባት ተፈጥሮ ተመልክተናል። በዚህም የቡድኑ የትጥቅ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ገብረመድህን እና የአወዳዳሪው አካል ተወካይ በሆኑት አቶ ጋሻው ረታ መካከል እሰጥ አገባ ተከስቶ ተመልክተናል። በመጀመሪያ የተካረረ እና ወደ ጉሽሚያ ሊያመራ የመስል የነበረው የሁለቱ ግለሰቦች ንትርክ እዛው በርዶ ብንመለከትም በቦታው የተገኘውን የስፖርት ቤተሰብ ትኩረት ለአፍታም ቢሆን ስቦ መታየቱ ተገቢ ነበር ማለት አንችልም።


© ሶከር ኢትዮጵያ