“አንድም ሰው ዞር ብሎ አላየኝም፤ ሊያሳክሙኝም አልፈለጉም” እዮብ ዓለማየሁ

በወላይታ ድቻ ከታዳጊ ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች መጫወት የቻለው እዮብ ዓለማየሁ አሁን ስላለበት ሁኔታ ይናገራል።

ከ17 ዓመት ታዳጊ ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ለወላይታ ድቻ ከፍተኛ አገልግሎት ሰጥቷል። ወጣቱ ፈጣን አጥቂ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ከዋናው ብሔራዊ ቡድን ውጭ በሁሉም የዕድሜ እርከን በሙሉ መጫወት ችሏል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከጉዳት ጋር ተያይዞ እየተቸገረ የሚገኘው እዮብ ዓለማየሁ በዘንድሮ ዓመት በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ ለወላይታ ድቻ ከተጫወተ በኋላ በደረሰበት ጉዳት በአሁን ሰዓት በቤቱ ይገኛል። ከወላይታ ድቻ ጋር የሚያቆየው ኮንትራት ቢኖረውም መቀነሱም ተነግሮታል። ይህ ሁኔታ እንዳሳዘነው ለሶከር ኢትዮጵያ ያለሁን ሁኔታ በዚህ መልኩ አቤቱታውን አቅርቧል።

” አንድም ቀን ጉልበቴን ሳልሳሳ ለወላይታ ድቻ መስጠት የሚገባኝን አገልግሎት ሰጥቻለሁ። የተጎዳሁትም በጨዋታ ሜዳ ነው። ይሆኖ ሳለ ካጋጠመኝ ጉዳት አገግሜ እያለው አሰልጣኙ ደውሎ መቀነሴን ነገረኝ። ቢሮ ላሉት አመራሮች በተደጋጋሚ ደውዬ እንዴት እንዲህ ይደረጋል ብዬ አቤቱታ አሰምቻለሁ። ቀሪ ኮንትራት አለኝ በዛ ላይ ክለቡ ሊያሳክመኝ ሲገባ አንድም ሰው ዞር ብሎ አላየኝም፤ ሊያሳክሙኝም አልፈለጉም። ደውለን እናወራሀለን ይሉኛል። ግን ማንም ምላሽ ሊሰጠኝ አልቻለም። ከቡድኑ ስለመቀነሴ እስካሁን በይፋ የደረሰኝ ደብዳቤ የለም። የክለቡን አመራሮች ለማግኘት ጥረቴን እቀጥላለሁ ይህ የማይሆን ከሆነም ጥያቄዬን ወደሚመለከተው አካል አደርሳለሁ ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ