ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

አሰልጣኞችን የተመለከቱ የትኩረት ነጥቦች እና አንኳር አስተያየቶችን እነሆ!

👉 መተንፈሻ ጊዜ ያገኙት ማሒር ዴቪድስ

ከጥቂት ሣምንታት በፊት በክለቡ አመራሮች የቡድኑን ውጤት እንዲያስተካክሉ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ደቡብ አፍሪካዊው ማሒር ዴቪድስ ከማስጠንቀቂያ በኃላ ቡድናቸውን ሀዲያ ሆሳዕናን ገጥሞ አቻ መለያየቱን ተከትሎ ጫና በርትቶባቸው ሰንብቷል። ይባስ ብሎ ክለቡ ሌላ አሰልጣኝ ለመቅጠር ዓይኑ ማማተር የመጀመሩ ዜና መሰማቱ በዚህኛው ሳምንቱ ቡድኑ አዳማን የገጠመበት ጨዋታ ለአሰልጣኙ እህል ውሃ እጅጉን ወሳኝ ከመሆኑ አንፃር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር። በጨዋታውም ቡድናቸው አዳማን 4-2 ማሸነፍ ችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አሰልጣኙ በከፍተኛ የደስታ ስሜት በተጠባባቂ ወንበር አካባቢ የነበሩ ተጫዋቾቻቸውን እና የአሰልጣኞች ቡድን አባላት እያጨበጡ ደስታቸውን የገለፁበት መንገድ አሰልጣኙ ከነበሩበትን ጫና አንፃር ያስመዘገቡት ውጤት የፈጠረባቸው የደስታ ስሜት የሚያሳይ ነበር።

አሰልጣኝ ማሒር ዴቪድስ የአዳማ ከተማው ድል በጥቂቱም ቢሆን የመተንፈሻ ጊዜን ቢያስገኝላቸውም በቀጣይ ይህን የማሸነፍ ጉዞ ማስቀጠል ካልቻሉ ግን አሁንም ቢሆን በቦታቸው የመቆየታቸው ነገር አጠያያቂ መሆኑ አይቀሬ ነው።

👉 ወደ ሥራ የተመለሱት አሰልጣኞች

ላለፉት ስድስት ወራት በተለያየ ምክንያት ክለብ አልባ የነበሩት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እና ፀጋዬ ኪዳነማርያም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግም በሜዳው ጠርዝ ሲዳማ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋርን እየመሩ ተመልክተናቸዋል።

በ2010 እና 11 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባለድል የሆኑት ገብረመድህን ኃይሌ ብዙ ተጠብቆበት በሚፈለገው ደረጃ መገኘት ያልቻለውን ሲዳማ ቡናን ወደ ቀደመ ተፎካካሪነቱ የመመለስን ኃላፊነት ሲረከቡ በተቃራኒው አሰልጣኝ ፀጋዬ እንደተሰረዘው የውድድር ዘመን ሁሉ የመውረድ ስጋት የተጋረጠበትን ጅማ አባጅፋርን በሊጉ የማቆየት ተልዕኮን ይዘው ወደ ሥራ ተመልሰዋል።

ሁለቱ የካበተ ልምድ ያላቸው የቀድው ተጨዋቾች በሁለተኛው ዙር በተወሰነ መልኩ የተረከቧቸውን ቡድኖች በሚፈልጓቸው ተጫዋቾች እና በተወሰነ መልኩም ቢሆን በሚፈልጉት የጨዋታ መንገድ ገንብተው ቡድኖች ምን ያህል ይዘዋቸው ይጓዛሉ የሚለው ጉዳይ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።

👉 በተቃራኒ የጨዋታ ሀሳብ የተፋለሙት አሰልጣኞች

በ12ኛው ሳምንት ከተደረጉ ጨዋታዎች ውስጥ የሊጉን በርካታ ግብ አስቆጣሪ ጥቂት ግቦችን በማስተናገድ ቀዳሚ ከሆነው ቡድን ጋር ያገናኘው ጨዋታ ይጠቀሳል ፤ ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዲያ ሆሳዕና። የሁለቱን ቡድኖች አሰልጣኞች የጨዋታ ምርጫ በግልፅ ያሳየው ፍልሚያም ያለግብ ተጠናቋል። ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ይጠበቅ እንደነበረው ኢትዮጵያ ቡናዎች ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥርን በመያዝ ሙከራዎችን ለማድረግ ክፍተትን ፍለጋ ሲማስኑ ሲውሉ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ በጥልቀት ተከላክለው አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር በመሞከር አሳልፈዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የተጋጣሚያቸው አቀራረብ እንደጠበቁት መሆኑ እንዳገዛቸው የተናገሩት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የጨዋታ ምርጫቸውን ከያዟቸው ተጨዋቾች ባህሪ አንፃር ጥቅም ላይ የዋለ መሆኑን ተናግረዋል። ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ጋናዊው የቡድኑ አማካይ ካሉሻ አልሀሰን ደግሞ ከሱፐር ስፖርት ጋር በነበረው ቆይታ ከአለቃው የተለየ ሀሳብን ሲሰነዝር እንደ ባርሴሎና የሚጫወቱ ቡድኖች እንዳሉ ሁሉ እንደ አትሌቲኮ ማድሪድ የሚጫወቱም ስለመኖራቸው ገልጿል። በተጋጣሚዎቻቸው ተመሳሳዩን ፈተና እየተጋፈጡ ያሉት አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በበኩላቸው ምንም እንኳን ሀዲያ ሆሳዕና ጥብቅ መከላከሉ ከግብ ቢያግዳቸውም ሙከራዎች ለማድረግ የሚረዱ ክፍተቶች የነበሩ መሆኑን አምነው የቅብብል ስኬት እና የአዕምሮ ግንኙነት መዳበር ለፈተናው ምላሽ መስጫ መንገዶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ዓበይት አስተያየቶች

👉 ፋሲል ተካልኝ ቡድኑ የሚያገኛቸውን የፍፁም ቅጣት ምቶች ስላለመጠቀሙ?

“ዛሬ የመጀመሪያ የፍፁም ቅጣት ምት መቺያችን ባዬ ነው። ጥሩ ግብ አግቢያችንም ነው። የፍፁም ቅጣት ምት በዕለቱ በመቺው የሚወሰን ነው። ዛሬ ነጥብ ላለማግኘታችን እሱን ብቻ ተጠያቂ አላደርግም። እርግጥ በመጨረሻ ሰዓት ጨዋታውን የምናሸንፍበት ዕድል ነበር። ግን እንደ ቡድንም በምንፈልገው መልኩ የጎል ዕድሎችን አልፈጠርንም።”

👉 ዘላለም ሽፈራው ስለ ቡድኑ የጨዋታ መንገድ እና ቀጣይ ጨዋታዎች?

ሁል ጊዜ በመልሶ ማጥቃት የምትጫወት ከሆነ ከፊት ያለው ተጫዋች በጣም ስለሚሮጥ ይደክምብሃል። በዚህ ላይ ደግሞ ጨዋታው የሚደረገው ቀጥር ላይ ስለሆነ ፀሀይ እና የአየር ሁኔታው ተፅዕኖ ይፈጥራሉ። ይህንን ተከትሎ ማስተካከል ያለብንን ነገር በቀጣይ እናስተካክላለን።

👉 ደግረገ ይግዛው ከጨዋታው ዳኝነት ጋር በተያያዘ?

“እኔም በጨዋታ ስሜት ውጥ ሆኜ ዳኝነቱን ስለምቆጣጠረው ይህ ነው ብሎ መናገር ይከብዳል። በእርግጥ ግን ጉልህ የነበሩ ስህተቶች ነበሩ። በተለይ የመስመር ዳኞቹ ላይ አንዳንድ ክፍተቶችን ስናይ ነበር። ስህተቶች ይኖራሉ። ግን በዚህ ደረጃ ዋጋ የሚያስከፍሉ ስህተቶች ትንሽ አስቸጋሪ ናቸው። ሆኖም ግን በትክክል ዳኞችን የሚገመግም አካል አለ ብዬ አስባለሁ። በተረፈ ግን ተጫዋቾቻችን ጫና ውስጥ እንዲገቡ እና ከጨዋታ መንፈስ እንዲወጡ አድርጓል። በአጠቃላይ ግን ከዛሬው ጨዋታ ብዙ ትምህርቶችን ይዘን ወጥተናል።”

👉አብርሀም መብራቱ በጨዋታው ሰለነበሩ ጉዳቶች?

“ከዚህ በፊት እንዳልኩት በቂ የፕሪሲዝን ጊዜ ያላሳለፉ ቡድኖች በውድድር መሐል እንደዚህ አይነት ችግሮች ያጋጥማቸዋል። ሌላኛው ደግሞ በጨዋታ መሐል የሚያጋጥሙ ግጭቶች ናቸው። እኔ እንደውም ይሄ ነገር ይቀጥላል ብዬ ነው የማስበው።”

👉ካሣዬ አራጌ ስለሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ

“ከውጤት አንፃር የምንፈልገውን አላገኘንም። ጨዋታውን ከመቆጣጠር አንፃር ግን ተቆጣጥረናል። ጨዋታ መቆጣጠር ብዙ ነገር ነው። የጎል እድሎችን የመፍጠር አጋጣሚ የምታገኝበት ነው። በተለይ ከእረፍት በኋላ አስራ አንዱም በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ነበሩ። ስለዚህ የመጫወቻ ሜዳዎች የጠበቡ ናቸው። በዛ ውስጥ ያለ የቅብብል ስኬት፣ የአዕምሮ ግንኙነት የመሳሰለው ነገር መዳበር አለበት። አንድ የምናስበው የተከፈቱ ቦታዎች አሉ። እሱን ግን በተገቢው መንገድ አልሰራንበትም። በአጠቃላይ ጨዋታውን ከመቆጣጠራችን አንፃር የምንፈልገውን ውጤት አግኝተናል ማለት አይቻልም።”

👉 አሸናፊ በቀለ በሁለተኛ አጋማሽ ማፈግፈግን ስለመምረጣቸው

“እንዲህ ለማድረግ የፈለግነው ያለንን አቅም በማገናዘብ ነው። የመጫወት አቅማቸው፣ ከኳስ ጋር ያላቸው ቁርኝት ስታስብ የምታጣቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። ቡናዎች ደግሞ ኳስ ካገኙ የመቀነስ አቅም አላቸው። ያንን የመጫወቻ ቦታ ማሳጣት ደግሞ ሌላው የኛ የታክቲክ አቀራረብ ነው። ስለዚህ ባቀድነው መሰረት ነው እነሱ የሄዱልን። እኛም ያሰብነውን ተግብረናል፤ የአጨራረስ ችግር ነው እንጂ። ወሳኝ የምንላቸው በጉዳት ያልገቡ ተጫዋቾች ቡድኔን ክፉኛ አሳስተውታል። በሚቀጥለው ተሟልተን ለመምጣት እንሞክራለን።”

👉 ገብረመድህን ኃይሌ ቡድኑ በመጀመሪያው ጨዋታ ስላሳየው እንቅስቃሴ

“ቡድኑን እያየሁት ነው። ገና ቡድኑን በደንብ እስካቀው ድረስ ሀሳብ መስጠት ያስቸግረኛል። ከዛሬው ጨዋታ በፊትም ለአራት ቀን ያህል ብቻ ነው ልምምድ የሰራነው። በአራት ቀን ልምምድ ለውጥ ማምጣትም ትንሽ ይከብዳል። ምንም ቢሆን ምንም ግን የዛሬው ጨዋታ ትምህርት ይሆነናል። የምንፈልገውን ቡድን ለመገንባት ግን ጊዜ ያስፈልገናል።”

👉ፀጋዬ ኪዳነማርያም ስለ ቀጣይ ጨዋታዎች?

“በቀጣይ የምንሰራቸው ሥራዎች አሉ። በተለይ እንደ ቡድን የበላይ ሆነን ጨዋታዎችን የምናረግበት መንገድ ላይ መስራት አለብን። እኔ ጎሎች በእንቅስቃሴዎች ውስጥ ሆነው እንዲገቡ እፈልጋለሁ። አሁን ላይ ያሉን ተጫዋቾች ውስን ናቸው። በጉዳት እና በኮንትራት ችግር አብረውን የማይገኙ ተጫዋቾች አሉ። ስለዚህ ይህንን ነገር አስተካክለን በቀጣይ በሚኖሩን የዕረፍት ጊዜያት እንደ ቡድን በደንብ ተጠናክረን እንቀርባለን።”

👉ማሂር ዴቪድስ ስለቡድናቸው የውድድር አጋማሽ ጉዞ

“በቡድኑ ውስጥ ብዙ መሻሻሎች አሉ። ብዙ የሚጠበቅብን ከመሆኑም አንፃር ልናሻሽላቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮች ነበሩ። የመጀመሪያውን እና የአሁኑን ጨዋታ የተመለከትን እንደሆን ግን ብዙ ለውጦች እንዳሉ መረዳት እንችላለን። በቀጣይም ከየጨዋታዎቹ ሙሉ ነጥቦችን ለማሳካት ጥረታችንን መቀጠል ይኖርብናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ