ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ከተማ ከጨዋታ ብልጫ ጋር አርባምንጭን ከተማን ረቷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የ12ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ አርባምንጭ ከተማን አስተናግዶ 5 ለ 1 አሸንፏል፡፡

ከአንድ ሳምንት በፊት የመኪና አደጋ ገጥሟቸው የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የነበራቸውን ጨዋታ በዚህ ምክንያት ማድረግ ሳይችሉ የአስራ ሁለተኛ ጨዋታ መርሐ ግብራቸውን ከአደጋው ነፃ ሆነው በተመለሱ ተጫዋቾች አማካኝነት አከናውኗል፡፡ ረፋድ 4፡00 ሲል በጀመረው ጨዋታ በሙሉ የጨወታው ክፍለ ጊዜ የሀዋሳ ከተማዎች ፍፁም የበላይነት የታየበት ነበር፡፡ አርባምንጭ ከተማዎች በአንፃሩ ኳሱን በሚይዙበት ወቅት ከርቀት ብቻ ሙከራን ሲያደርጉ የተስተዋለ ሲሆን ቀስ በቀስ በሀዋሳ ብልጫ እየተወሰደባቸው ሲመጣ ግን የነበራቸውን መልካም አጀማመር ማስቀጠል ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ከመሀል ሜዳ በሚገኙ የተቀናጁ የቅብብል ሒደቶች ወደ አርባምንጭ የግብ ክልል ሳይቸገሩ በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት ሀዋሳዎች 8ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል፡፡ ካሰች ፍሰሐ በቀኝ የአርባምንጭ የግብ ክልል ከሳጥን ጠርዝ ወደ ጎል የላከችውን ኳስ ረድኤት አስረሳኸኝ እግር ስር ስትደርስ ተጫዋቿ በቅርብ ርቀት ለነበረችሁ ዙፋን ደፈርሻ ሰጥታት አማካይዋም ወደ ጎልነት አጋጣሚዋን ለውጣዋለች፡፡

ሰናይት ባሩዳ ካደረገችው የቅጣት ምት ሙከራ ውጪ በሀዋሳ ለመበለጥ የተገደዱት አርባምንጮች በድጋሚ በተከላካዮቻቸው ስህተት ሁለተኛ ጎልን አስተናግደዋል፡፡ ረድኤት አስረሳኸኝ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የተሻገረላትን ኳስ በደረቷ አብርዳ ሁለት ጊዜ ብቻ ገፋ አድርጋ ወደ ሳጥን ከገባች በኃላ በድንቅ አጨራረስ ከመረብ አዋህዳ 2 ለ 0 ሀዋሳን አሸጋግራለች፡፡

ካለፉት ጨዋታዎቻቸው በመሀል ሜዳ ላይ የመቅደስ ማሞ እና ዙፋን ደፈርሻን አስገራሚ ቅንጅት በሚገባ ሲጠቀሙ የታዩት ሀዋሳዎች በዚህ የጨዋታ ቦታ የወሰዱት የበላይነት ሶስተኛ ጎል አሁንም እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ 27ኛው ደቂቃ ላይ የቀኝ መስመር ተከላካዩዋ ፀሀይነሽ ጁላ የሰጠቻትን ኳስ አሁንም ረድኤት አስረሳኸኝ ያገኘችሁን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀም ወደ ጎልነት ለውጣው ሀዋሳን 3ለ0 አድርጋለች ተጫዋቿም ለራሷ ሁለተኛ ለክለቧ ሶስተኛ ጎል ሆኖ ተመዝግቦላታል፡፡

ሀዋሳዎች በቀሩት ደቂቃዎ በካሰች ፍሰሀ እና በረድኤት አስረሳኸኝ አማካኝነት ተጨማሪ የጎል ዕድሎችን የሚፈጥሩበትን አጋጣሚዎች ቢፈጥሩም ወደ ጎል መለወጥ ሳይችሉ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ አሁንም የሀዋሳ ከተማ የበላይነት የተንፀባረቀበት የነበረ ቢሆንም አርባምንጭ ከተማዎች ወጥነት ይጎላቸው ስለነበረ እንጂ በተወሰነ መልኩ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ለመንቀሳቀስ ጥረት አድርገዋል፡፡ የሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ አራት ያህል ደቂቃ ብቻ እንደተቆጠረ ተቀይራ የገባችው ትውፊት ካዲኖ ጣጣውን የጨረሰ ኳስ መሀል ለመሀል አሾልካ ሰጥታት አጥቂዋ ነፃነት መና በአግባቡ ተጠቅማበት የሀዋሳን የጎል መጠን አስፍታለች፡፡56ኛው ደቂቃ አርባምንጭ ከተማዎች ወደ ጨዋታ ልትመልሳቸው የምትችልን ጎል አግኝተዋል፡፡ በቤተል ጢባ ላይ ትዝታ ኃይለ ሚካኤል በሀዋሳ የግብ ክልል የሰራችውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት የቀድሞዋ የደደቢት እና ንግድ ባንክ አጥቂ ሰናይት ባሩዳ አክርራ በመምታት አጋጣሚን በአግባቡ ተጠቅማ አርባምንጭን ወደ 4 ለ 1 አሸጋግራለች፡፡

ጎል ካስቆጠሩ በኃላ አርባምንጮች መነቃቃት ይታይባቸዋል ተብለው ቢጠበቁም በተቃራኒው አምስተኛ ጎልን አስተናግደዋል፡፡ በግምት ከ35 ሜትር ርቀት ላይ ወደ ግራ ባደላ ቦታ ሀዋሳዎች ያገኙት የቅጣት ምት ተቀይራ የገባችው አጥቂዋ መሳይ ተመስገን በግሩም ሁኔታ የአርባምንጯ ግብ ጠባቂ ነህሚያ አብዲ ስህተት ታክሎበት ከመረብ አሳርፋለች፡፡ ሀዋሳዎች በካሰች ፍሰሀ አማካኝነት ሶስት ጊዜ አስቆጪ ዕድሎችን ቢያገኙም የመስመር ተከላካዩዋ ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም ሳትችል ጨዋታው 5 ለ 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡

አምስተኛው ደቂቃ ላይ የዕለቱ ዋና ዳኛ ምስጋና ጥላሁን የሀዋሳ ተጫዋቾች ኳስን ለማቀበል ባደረጉበት ቅፅበት ኳሷ ዳኛዋን ነክታ ሜዳ ላይ የወደቀችበት አጋጣሚ ብዙሀኑን ፈገግ ያሰኘች ሁነት ነበረች፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሀዋሳ አማካይ ዙፋን ደፈርሻ የጨዋታው ምርጥ ተብላ በልሳን የሴቶች ስፖርት ተመርጣለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ