የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 1-0 ጅማ አባ ጅፋር

የረፋዱ ጨዋታ በሀዲያ ሆሳዕና 1-0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለውጤቱ

ብናሸንፍም አጠቃላይ በጨዋታው የኘበረው እንቅስቃሴ በተመልካቹም በእኔም በኩል እርካታ ያለው አልነበረም። ለማረም እንሞክራለን እንጂ እግዶች የበዙበት ጨዋታ ነው። ስለዚህ ውጤቱ እንዳለ ሆኖ በፍፁም አርኪ እንቅስቃሴ አልነበረም።

ለቡድኑ ግብ የማስቆጠር ችግር

ከጅማ ጀምሮ ብዙ መሰናክሎች ነበሩብን። የነገሮች አለመስተካከል ፣ የተጨዋቾች ጤና መጓደል እና ተሟልቶ አለመግባት፤ ምክንያት ይሆንብኛል እንጂ ዛሬም አምስት ያህል ቋሚ ተሰላፊዎች አልነበሩም። እነዚህን ነገሮች ለማስተካከል አንደኛ ክፍተቶችን መድፈን ይፈልጋል። ተጠባባቂ ላይ ያገኘናቸው ተጫዋቾችም ሁለት ቢሆኑ ነው። ሌሎቹ ምን ያህል ጠቃሚ ነበሩ የሚለውም አጠያያቂ ነው። ቡድኑን ወደ ተሻለ ሁኔታ ለመውሰድ የሰው ኃይል አስፈላጊ ነው። ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ቢስተካከል መልካም ነው ብዬ አስባለሁ።

ቡድኑ በቀጣይ የአጨዋወት ለውጥ ያደርግ እንደሆነ

ያሉት ተጨዋቾች ይወስኑታል። የፈለከውን ፍልስግና ለመተግበር የልጆቹ አቅም ወሳኝ ነው። ለምሳለ ተከላካይ ቦታ ላይ ያሉ ልጆች የኳስ ክህሎታቸው ጥሩ ካልሆነ ተጫወቱ የምትለው ነገር አደጋ ያመጣል። ከዚህ አንፃር የተጎዱብን አምስት ተጫዋቾች ሲመጡ ይስተካከላል ብዬ ተስፋ አሰርጋለሁ።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባ ጅፋር

ስለ ጨዋታው እና ውጤቱ

የምንፈልገውን ለማሳካት የግድ በእያንዳንዱ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ማግኘት ያስፈለግ ነበር። ዛሬ ሁለታችንም በከፍተኛ ተነሳሽነት እልህ የተሞላበት ጨዋታ ተጫውተናል። በተጨመረ ደቂቃ ነው ጎል የገባው። እግርኳስን ተወዳጅ ያደረገውም ይህ ነው። በጨዋታው እነሱም እኛም ግልፅ የግብ እድሎች አግኝተናል። ጠንካራ ጨዋታ ነበር። ግን እንደ ቡድን ሦስት ነጥቡን መነጠቅ አልነበረብንም። አቻ ተገቢው ውጤት ነበር ብዬ አስባለሁ። ውጤቱን በፀጋ ተቀብለን ለቀጣይ ጨዋታ መዘጋጀት ነው።

ስለ ዝውውር መስኮት

ተጫዋቾችን ማምጣት የግድ ነው። ክፍተቶች ባሉበት ቦታ ላይ ተጨማሪ ተጫዋቾች ለማግኘት እንሞክራለን። በእርግጥ ያናገርናቸው ተጫዋቾች ከእጃችን እያመለጡ ነው ያሉት። ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ አላወቅኩም። ዞሮ ዞሮ ስር ነቀል ሳይሆን ቡድኑን ለማጠናከር ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ