ለወልቂጤ የተስፋ ቡድን የገንዘብ እና የትጥቅ ድጋፍ ተደረገላቸው

በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ እየተሳተፉ የሚገኙት የወልቂጤ ተስፋ ቡድን አባላት የገንዘብ እና የትጥቅ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

የከተማው አስተዳደር ትኩረት ተነፍጓቸው በዚህ ዓመት የመወዳደራቸው ነገር ያከተመለት መስሎ የነበረው የወልቂጤ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውድድሩ ከተጀመረ በኃላ በአቶ አበባ ሰለሞን (የክለቡ ምክትል ፕሬዝደንት) የግል ተነሳሽነት ለቡድኑ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገው እየተወዳደሩ ይገኛል።

አስቀድሞ የመመዝገቢያ የትራንስፖርት እና ውድድሩ በሚካሄድበት አዳማ ከተማ ለሚኖራቸው የአንድ ወር ቆይታ ለሚያርፉበት ሆቴል የምግብ እና የመኝታ በግምት ወደ 70 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ድጋፍ አድርገዋል።

ከሰሞኑ ደግሞ አቶ አበባው ተጫዋቾቹ ወደሚገኙበት ከተማ በማቅናት በስነ ልቦናው ጠንካራ እንዲሆኑ እና የውድድሩ ግብ ውጤት ወይም ዋንጫ ማንሳት ሳይሆን ለዋናው ቡድን ተተኪ ትውልድ ማፍራት ስለሆነ በርትተው እዲሰሩ በመመክር በቡድን ውስጥ አለ የሚባለውን ችግር ከሰሙ በኃላ ለትጥቅ ለኳስ እና ሌሎች ለሚያስፈልጉ ነገሮች ከ50 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ድጋፍ አድርገውላቸዋል።

የቡድኑ አሰልጣኝ አንዋር ” ዞር ብሎ የሚያየን በልነበረበት ሰዓት ከውድድር መመዝገቢያ ወጪ ከመሸፈን ጀምሮ አሁን ያረፍንበት ሆቴል ድረስ በመምጣት ከመምክራቸው በተጨማሪ የነበረብን የትጥቅ ችግር ተመልክቶ የገንዘብ ድጋፍ በማድረጋቸው በቡድኑ አባላት ስም ምስጋና እናቀርባለን። ወደፊትም ይህ በጎ ድጋፍህ እንዳይለየን።” በማለት ተናግረዋል።

አቶ አበባው ሰለሞን ለወጣት ተጫዋቾቹ ያደረጉት ተግባር በመልካምነቱ የሚጠቀስ ሲሆን መሰል ባለሀብቶችም ትኩረት በተነፈገው የታዳጊ እግርኳስ ላይ ትኩረት አድርገው ለሚሰሩ ክለቦች ድጋፍ ቢያደርጉ መልካም ነው እንላለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ