ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዳማ ከተማ በወይንሸት ፀጋዬ ብቸኛ ጎል አዲስ አበባን አሸንፏል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የአስራ ሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ በአዳማ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ መካከል ተደርጎ አዳማ 1ለ0 አሸንፎ ወጥቷል፡፡

በረዳት አሰልጣኟ የሺሃረግ ለገሰ መሪነት ወደ ሜዳ የገቡት አዲስ አበባ ከተማዎች ከዋና አሰልጣኟ ሙሉጎጃም እንዳለ እገዳ በኋላ ጨዋታ አድርጓል። በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አዳማ ከተማዎች በተሻለ የማጥቃት ሀይል ወደ ሜዳ መግባት የቻሉ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማዎች በአንፃሩ ኳስን ይዘው ወደ አጥቂ ክፍሉ በሚያሻግሩበት ወቅት ደካማ የፊት መስመርን ይዘው በመቅረባቸው የተለየ ነገርመፍጠር አልቻሉም፡፡

አዳማ ከተማዎች 8ኛው ደቂቃ በሰብለ ቶጋ የቅጣት ምት ኳስ የመጀመሪያ ሙከራን በማድረግ ወደ አዲስ አበባ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን ከ13ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ በፈጠሩት የመልሶ ማጥቃት ፈጣን ሽግግር ጎል አስቆጥረዋል፡፡ ከቀኝ የአዲስ አበባ የግብ አቅጣጫ በረጅሙ የተሻገረን ኳስ ሰርካዲስ ጉታ በግንባሯ ነካ አድርጋ ለወይንሸት ፀጋዬ ሰጥታት ተከላካዩዋም ወደ ጎልነት ለውጣው አዳማ ከተማን መሪ አድርጋለች፡፡

አምበሏ ትርሲት መገርሳ ከቅጣት ምት ከቅጣት ምት ካደረገችው ሙከራ ውጪ በእንቅስቃሴ ጥሩ ቢሆኑም ወደ ጎል መድረስ የተቸገሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ረጃጅም ኳሶችን መጠቀማቸው ተጠቃሚ ሲያደርጋቸው አልታየም፡፡ ይልቁኑም አዳማ ከተማዎች ተጨማሪ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ዕድሎችን በተለይ ከፈጣኗ አጥቂ ሰርካለም ጉታ አግኝተው ተጫዋቿ መረጋጋት ተስኗት መጠቀም ሳትችል ቀርታለች፡፡

ከእረፍት መልስ አዲስ አበባ ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ ድክመታቸው በሚገባ ተሻሽለው የቀረቡበት ሲሆን በፈጣን የመስመር አጨዋወት ወደ ጨዋታ ለመመለስ ብርቱ ትግል ማድረግ ቢችሉም ኳስን መረብን የሚያገናኝ ተጫዋች በቡድኑ ውስጥ አለመኖሩ ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው ጥሩ ጊዜን ማሳለፍ ባይችሉም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገባ ተፈትነው ባደረጉት ብርቱ የማስጠበቅ ሂደት በመጨረሻም ተሳክቶላቸው፡፡ ጨዋታው 1 ለ 0 ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የማሸነፍያ ጎሏን ከመረብ ያሳረፈችው ወይንሸት ፀጋዬ የልሳን የሴቶች ስፖርት የጨዋታ ምርጥ በመባል ተሸልማለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ