የከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ የመጀመርያው የውድድር ዘመን አጋማሽ ዛሬ ተጠናቀቀ

የከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ የመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ ሲካሄድ ሀምበሪቾ ዱራሜ፣ ሻሸመኔ ከተማ እና ሀላባ ከተማ በድል ዙሩን አጠናቀዋል።

ጠዋት 04:00 የጀመረው ቤንች ማጂ ቡና እና ሀምበሪቾ ዱራሜ ጨዋታ በሀምበሪቾ አራት ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል። በቤንች ማጂ አንበል በኩል የተጫዋች ተገቢነት ክስ በማሲያዝ የተጀመረው ጨዋታ ጥሩ ፍሰት ያለው እግርኳስ አስመልክቶን ተጠናቋል። በሁሉም ረገድ የተሟላ ቡድን መሆኑን ያሳየን ሀምበሪቾ ገና በጨዋታው ጅማሬ ከመስመር ሰብሮ ወደ ሳጥን የገባው አልአዛር አድማሱ ከእርሱ በተሻለ ጥሩ አቋቋም ለሚገኘው ለቡድን አጋሩ ፀጋአብ ዮሴፍ ማቀበል የሚችለው ኳስ ራሱ ለመጠቀም አስቦ በግቡ ቋሚ ታኮ በወጣው ሙከራ የመጀመርያውን የጎል ዕድል ፈጥረዋል። ሀምበሪቾዎች ከመስመር በሚነሱ ኳሶች አደጋ መፍጠራቸውን ቀጥለው ሌላ ጎል መሆን የሚችል ዕድል ዳግም በቀለ አግኝቶ በማይታመን ሁኔታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ሀምበሪቾዎች ኳሱን አደራጅተው ወደፊት ለመግባት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚበላሹ ኳሶችን ፍለጋ ትኩረት በማድረግ በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር ያሰቡት ቤንች ማጂዎች ግልፅ የጎል አጋጣሚ አይፈጥሩ እንጂ ለተከላካዮች ፈተኛኝ ሲሆኑ አስተውለናል።

እንደወሰዱት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ከጎል ጋር የተራራቁት በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚሰለጥኑት ሀምበሪቾዎች ከዕረፍት መልስ የሳሳውን የአጥቂ ክፍል ለማጠናከር ቢንያም ጌታቸው እና አምረላ ደልታታን በፍጥነት ቀይረው በማስገባት የወሰኑት ውሳኔ ተሳክቶላቸው በ58ኛው ደቂቃ የጨዋታውን ልዩነት የፈጠረ ጎል ቢንያም ጌታቸው በጥሩ ሁኔታ አስቆጥሯል። ከዚህች ጎል መቆጠር በኃላ የአቻነት ጎል ፍለጋ ተጭነው መጫወት የቻሉት ቤንች ማጂዎች ግልፅ የጎል ዕድል ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት የሀምበሪቾ ጠንካራ የመከላከል አቅምን መስበር ባለመቻላቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

የዕለቱ ዳኛ በእያንዳንዱ ድርጊት ካርድ መምዘዛቸው የጨዋታውን ፍሰት ቢያቀዘቅዘው በመጨረሻው አስር ደቂቃ ጨዋታው በጎል የታጀበ ሆኗል። ተቀይሮ በመግባት የሀምበሪቾ የማጥቃት አቅም የጨመረው ብሩክ ኤልያስ በ82ኛ እና በ90ኛው ደቂቃ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር የጎሉን መጠን ወደ ሦስት አድርሶታል።

የቤንች ማጂ ቡናው ተከላካይ ጌታሁን ገላዬ ከዳኛው ጋር በፈጠረው ሰጣ ገባ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከተወገደ በኃላ ከመስመር ብሩክ ኤልያስ አመቻችቶ ያቀበለውን ቢንያም ጌታቸው አራተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በሀንበሪቾ 4-0 ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቀትር ላይ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ባለበት ሁኔታ የተካሄደውና ሻሸመኔ ከተማን ከወላይታ ሶዶ ያገናኘው ጨዋታ በሻሸመኔ ከተማ 3-0 አሸነፊነት ተጠናቋል።

ተመጣጣኝ ፉክክር እያስመለከተን የመጀመርያ አስራ አምስት ደቂቃ ቢቆይም ኃላ ላይ ሻሸመኔዎች የኳስ ቁጥጥሩን ብልጫውን በመውሰድ የጎል እድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም ክፍት ቦታ ባለማግኘተቻው ከርቀት ጎል በመፈለግ ከሳጥን ውጭ አዲስዓለም ደሳለኝ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ አንግሉን ታኮ ሊወጣበት ችሏል። በወላይታ ሶዶ በኩል ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከቀኝ መስመር አፈትልኮ የገባው ሰለሞን ጌታቸው ነፃ አቋቋም ለሚገኘው አላዛር ፋሲካ አቀብሎት ወደ ጎል ቢመታው ተከላካዮቹ እንደምንም ተደርበው ያወጡበት የሚያስቆጭ ሙከራ ነበር።

ከዕረፍት መልስ የአየሩ ሁኔታ የከበዳቸው በሚመስል መልኩ ቡድኖቹ ተዳክመው የተመለከትን ቢሆንም ሻሸመኔ ከተማዎች በ52ኛው ደቂቃ አዲስዓለም ደሳለኝ በራሱ ጥረት ወደ ሳጥን ኳሱን በመግባት የመጀመርያውን ጎል አስቆጥሯል።

ከጎሉ መቆጠር በኃላ ጨዋታው ተጋግሎ በወላይታ ሶዶ በኩል በግሉ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የዋለው አማካይ ሰለሞን ጌታቸው ወደ ጎል የመታውን የሻሸመኔው ግብጠባቂው ግዛቸው ሀብቴ በጥሩ ሁኔታ አዳነበት እንጂ ሶዶዎችን ወደ ጨዋታው የምትመልስ አጋጣሚ ነበረች። በዚህ የጎል ሙከራ የተደናገጡት ሻሸመኔዎች በፍጥነት አፀፋዊ ምላሽ በመስጠት በ57ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተደርቦ እግሩ የገባውን ኳስ ከድር ሁሴን ወደ ጎልነት በመቀየር ጨዋታውን እንዲቆጣጠሩ አስችሏቸዋል።

ብዙም የተለየ ነገር ሳንመለከት ጨዋታው ቀጥሎ ተቀይሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ልዩ ሆኖ የዋለው አዲስዓለም ከመስመር በመነሳት ተከላካዮችን አታሎ ያመቻቸውና አሸናፊ ጥሩነህ ነፃ ኳስ አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ዕድል ጥሩ አጋጣሚ ነበር። በመጨረሻው ጭማሪ ደቂቃ በራሱ ላይ የተሰራውን ጥፈት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ማናዬ ፋንቱ ወደ ጎልነት ቀይሮት ጨዋታው በሻሸመኔ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የውድድር ዓመቱ አጋማሽ የመጨረሻ ጨዋታ አስር ሰዓት ላይ አቃቂን ከ ሀላባ ያገናኘው ሲሆን በሀላባ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል። ከቅብብሎሽ ባለፈ በርከት ያሉ የጎል ሙከራ ያልታጀበ የነበረው ይህ ጨዋታ አቃቂዎች የመጀመርያውን የጎል ዕድል በእስማኤል አደም አማካኝነት መፍጠር ቢችሉም ለጥቂት ሳይሳካ ቀርቷል። መሐል ሜዳ ላይ ብቻ ተገድቦ የቀጠለው ጨዋታ በእንቅስቃሴ ሳይሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚፈጠሩ ዕድሎች ሁለቱም ቡድኖች ጎል ለማግባት የሚያደርጉት ጥረት ለሀላባዎች ተሳክቶ በ30ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ውብሸት ሥዩም በመምታት የሀላባን ቀዳሚ ጎል አስቆጥሯል።

ከዕረፍት መልስ አቃቂዎች በተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ግልፅ የጎል ዕድል ያልፈጠረ በመሆኑ ብልጫቸው ትርጉም አልባ ሲሆን ይልቁንም ሀላባዎች መሪነታቸውን ማጠናከር የሚችሉበትን እድል ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር የሚችልበትን አጋጣሚ ውብሸት ሥዩም ቢፈጥርም የአቃቂው ግብጠባቂ አዝማች ወልደ ገብርኤል በአስደናቂ ብቃት አድኖበታል።

ጥንቃቄ የመረጡት ሀላባዎች ወደ ኃላ ማፈግፈጋቸውን ተከትሎ አቃቂዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ ተጭነው ቢጫወቱም በተመሳሳይ መንገድ የሚያደርጉት የማጥቃት መንገዳቸው በሀላባ ተከላካዮች በቀላሉ ሲመለስባቸው ተስተውሏል። ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት የፈለጉት ሀላባዎች ሀሳባቸው ተሳክቶላቸው ጨዋታውን አንድ ለምንም አሸንፈው መውጣት ችለዋል።© ሶከር ኢትዮጵያ