ሪፖርት| ድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

በ13ኛው ሳምንት የመጨረሻ የጨዋታ ቀን ድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ያለ ጎል ጨዋታቸውን ፈፅመዋል።

አዲሱ የድሬዳዋ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ቡድኑ በጅማ ቆይታው በፋሲል ካስተናገደው ስብስብ ምንያምር ጴጥሮስን በያሬድ ዘውድነህ እንዲሁም አስጨናቂ ሉቃስን በእንዳለ ከበደ በመለወጥ ጨዋታውን የጀመሩ ሲሆን አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በተመሳሳይ ከቀናት በፊት በፋሲሉ ከተሸነፉበት ጨዋታ የአራት ተጨዋቾች ለውጥ በማድረግ ዳንኤል ደርቤ ፣ ዮሐንስ ሴጌቦ ፣ ኤፍሬም ዘካርያስ እና አለልኝ አዘነን በመተካት ፀጋአብ ዮሐንስ ፣ ደስታ ዮሐንስ ፣ ጋብርኤል አህመድ እና ወንድምአገኝ ኃይሉ ወደ መጀመሪያው አሰላለፍ መጥተዋል።

በሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሳቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ ያልታየበት ጨዋታው በዳኛ ፊሽካ የሚቆራረጥ እና ጠንካራ ሙከራዎች ያልነበሩበት ነበር።

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የሀዋሳ ተከላካዮችን ጀርባ በመጠቀም ጥቃት ለመሰንዘር የጣሩት ድሬዎች በአንፃራዊነት የተሻለ አጋጣሚዎች መፍጠር የቻሉ ሲሆን በሦስተኛው ደቂቃ ዘነበ ከበደ ያሻገረውን ኳስ ሙኅዲን በፍጥነት ከተከላካይ ጀርባ አምልጦ በመግባት ጥሩ አቋቋም ላይ ወደነበረው ናንጄቦ ለማሻገር ቢሞክርም ለመጀመርያ ጊዜ ተሰላፊ ሆኖ የገባው ፀጋአብ ተደርቦበት ቋሚውን ታኮ የወጣበት መልካም አጋጣሚ ነበር።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ቅኝት ለመግባት የሞከሩት ሀዋሳዎች ኳስ በመቆጣጠር ጥቂት የማግባት አጋጣሚዎችን በመጀመርያው አጋማሽ መፍጠር ችለዋል። በ16ኛው ደቂቃ ጋብሬል ከርቀት አክርሮ መትቶ በግቡ አናት ወደ ውጪ የወጣበት እንዲሁም በ23ኛው ደቂቃ ብሩክ በየነ በጥሩ ሁኔታ በተጫዋቾች መሐል አልፎ ወደ ሳጥን በመግባት ከግራ አቅጣጫ ወደ ግብ የላከው ኳስ የግብ ጠባቂው እና ተከላካዮች ርብርብ የወጣበት ዕድሎች የሚጠቀሱ ነበሩ።

ከዕረፍት በኋላም የተለየ መልክ ያልነበረው ጨዋታው ከቆሙ ኳሶች ከሚፈጠሩ ዕድሎች ካልሆነ በቀር የተደራጀ እና የጎላ የማጥቃት እንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል አልታየበትም። በዚህም በሀዋሳ በኩል በ 58ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት በፍጥነት የተሻማውን ኳስ ምኞት ሞክሮ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡት እንዲሁም በድሬዳዋ በኩል በ84ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ጁኒያስ ናንጄቦ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት ሙከራ ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉ ብቸኛ የሁለተኛ አጋማሽ ዕድሎች ነበሩ።

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሀዋሳ በነበረበት ሰባተኛ ደረጃ ላይ ሲረጋ ድሬዳዋ ከተማ የወራጅ ቀጠናውን ከሰዓት ጨዋታ ለሚያደርገው ሲዳማ ቡና አስረክቦ አስረኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ