የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

የ13ኛው ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ትኩረት ሳቢ የተጫዋች ነክ ጉዳዮችን ተመልክተናል።

👉 ሦስት ሐት-ትሪክ በግማሽ የውድድር ዘመን – አቡበከር ናስር

በ2013 የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአቡበከር ናስር ደረጃ እየደመቀ የሚገኝ ተጫዋች ፈልጎ ማግኘት የማይታሰብ ነው። ወጣቱ አጥቂ የእስካሁኑ የእግርኳስ ህይወቱ እጅግ ምርጡን የውድድር ዘመን እያሳለፈም ይገኛል።

ኢትዮጵያ ቡና አዳማ ከተማን 4-1 ሲረታ የውድድር ዘመኑን ሦስተኛ ሐት-ትሪክ መስራት የቻለው ተጫዋቹ በ13 የሊግ ጨዋታዎች 17 ግቦችን በማስቆጠር የሊጉን ከፍተኛ አስቆጣሪነት እየመራ ሲገኝ ከተከታዩ ሙጂብ ቃሲም ደግሞ በአምስት ግቦች ከፍ ብሎ መቀመጥ ችሏል።

በአማካይ በጨዋታ 1.3 ግቦችን እያስቆጠረ የሚገኘው አቡበከር በሊጉ ከሚገኙት 9 ቡድኖች የላቀ መጠን ለብቻው ያስቆጠረ ሲሆን በዚህ ሒደቱ የሚቀጥል ከሆነ በንፅፅር በቁጥር አነስተኛ ተካፋይ ቡድኖችን በያዘው የዘንድሮው የሊግ ውድድር በአንድ የውድድር ዓመት በርካታ ጎሎች ያስቆጠረ ተጫዋች የመሆኑ ነገር የሚቀር አይመስልም።

👉 የለዓለም ብርሀኑ ስህተቶች
በሸገር ደርቢ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ቡና በተረታበት ጨዋታ ገና በጨዋታው ጅማሮ ኬንያዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ ቀይ ካርድ መመልከቱን ተከትሎ ለአንድ ዓመት ያህል ከሜዳ ካራቀው ጉዳት መልስ ወደ ጨዋታ የተመለሰው ለዓለም ብርሃኑ አሁን ድረስ የቀደመውን ብቃቱን ፍንጭ ማሳየት እንደተሳነው ቀጥሏል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍ ያለ ግምት ከሚሰጣቸው ግብ ጠባቂዎች አንዱ የነበረው ለዓለም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመጣ ወዲህ በመሰለፍ ዕድል እጦት ብቃቱ መውረድ ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። ታድያ ይህም እውነታ ከገጠመው አስከፊ ጉዳት ጋር ተያይዞ ቡድኑ ግልጋሎቱን አጥብቆ በሚሻበት ወቅት በሚጠበቅበት ደረጃ ከማገልገል ይልቅ አንገት የሚያስደፉ ተደጋጋሚ ስህተቶችን እየሰራ ይገኛል።

ውሳኔዎቹ ላይ እርግጠኝነት የራቁት ተጫዋቹ ኳሶች በሚይዝበትም ሆነ ኳሶችን ለመያዝ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ አንዳች ግራ የመጋባት ስሜት ይነበብበታል። በመጀመሪያው ጨዋታ በቡና ሲረቱ የሰራው ስህተት ቡድኑን ለሽንፈት ሲዳርግ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማ ያስቆጠሯቸው የመጨረሻ ሁለት ግቦች በቀጥታ የእሱ ስህተቶች ውጤት ነበሩ።

እርግጥ ነው ግቦቹ በተቆጠሩበት መንገድ እንደ ቡድን የመከላከል አወቃቀሩ ላይ ጥያቄ ቢያስነሳም ለዓለም የሰራቸው ከመሠረታዊ የግብ ጠባቂ ክህሎት የራቁ ስህተቶች ግን ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አልነበሩም። ስለሆነም ተጫዋቹ በእነዚህ ስህተቶች አንገቱን ሳይደፋ የቀደመ ብቃቱን ዳግም ለማግኘት ይበልጥ መታተር ያለበት ወሳኝ ወቅት ላይ ይገኛል።

👉 ፈቱዲን ጀማልን ምን ነካው ?

ተቀዳሚ አምበላቸው ግርማ በቀለ ወደ ተጠባባቂ ወንበር መውረድን ተከትሎ የሲዳማ ቡናን የአምበልነት ማዕረግ የተረከበው ፈቱዲን ጀማል በጥቂት የጨዋታ ሳምንታት ልዩነት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ለመወገድ በቅቷል። ይህ ጉዳይ ከተጨዋቹ የቀደመ የተረጋጋ ባህሪ እና የጨዋታ አካሄድ አንፃር ሲታይ ‘ፈቱዲንን ምን ነካው ?’ የሚያስብል ሆኖ አግኝተነዋል።

እርግጥ ነው ብዙ ተጠብቆበት በሚፈለገው ደረጃ መገኘት ያልቻለው ስብስብ ውስጥ በሚገኙ ተጫዋቾች ውስጥ ተከታታይ ውጤት አልባ ጉዞዎች የሚፈጥሩት የሥነ-ልቦና ጫና ከምናስበው በላይ ከባድ መሆኑ ቢታመንም ቡድኑን በአምበልነት የሚመራው ተጫዋች ግን ይህን በሥነ-ልቦና ረገድ የተጎዳውን ስብስብ በማነሳሳት ወደ ውጤት ለመምራት መጣር እንጂ በረባ ባረባ ከዳኞች ጋር እሰጥ አገባዎችን መፍጠር ብሎም በተዳከመው የቡድኑ ስብስብ ላይ ቡድኑን ለቀጣይ ጨዋታዎች አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ ተደጋጋሚ ካርዶችን መመልከት እጅግ ያልተገባ ድርጊት ነው።

ፈቱዲን ከጥቂት የጨዋታ ሳምንታት በፊት ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ሲጋራ ከዳኛ ጋር በፈጠረው በአላስፈላጊ ጭቅጭቅ ምክንያት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሲወገድ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት እንዲሁ በድቻ ሲሸነፉ መሀል ሜዳ ላይ በሰራው ያልተገባ ጥፋት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሊወጣ ችሏል።

👉 የአቤል እንዳለ ዳግም ማንፀባረቅ

ከቀናት በፊት በፈረሰኞች መለያ የመጀመሪያውን ግብ ማስቆጠር የቻለው አማካዩ አቤል እንዳለ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ለሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ላይ አንድ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ለረጅም ጊዜያት በተጠባባቂ ወንበር ያሳለፈው አማካዩ አሰልጣኝ ማሒር ዳቪድስ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከቀድሞ የደደቢት አጣማሪው ያብስራ ተስፋዬ ጋር በፈረሰኞቹ የመሀል ሜዳ ላይ የተሰጣቸውን የመሰለፍ ዕድል በአግባቡ እየተጠቀሙ ይገኛል።

ከወትሮው በተለየ በማጥቃት ሂደቶች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ መገኘት የጀመረው አቤል ቀድሞ ይታወቅበት የነበረውን በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ተጫዋቾች እየቀነሰ ኳሶችን ወደ ሜዳው የላይኛው ክፍል ይዞ የመግባት እና የመጨረሻ ኳሶችን የማቀበል ብቃቱን ዳግም እያገኘ ይመስላል። ሁለቱም ያስቆጠራቸው ግቦች በዚህ ሂደት የተገኙ መሆናቸው ተጫዋቾቹ ከጨዋታ በመራቁ አጧቸው የነበሩት ብቃቶቹን ዳግም እያገኘ ስለመሆኑ ማሳያ ይሆናሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህኛው ሳምንት ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ ለመውጣት መገደዱ የተጨዋቹ ቀጣይ ፈተና ይመስላል። ምንም እንኳን ከረጅም ጊዜ ተጠባባቂነት በኋላ ዕምነት ተጥሎበት ብቃቱን የማሳየት አጋጣሚው ቢከፈትለትም በጉዳቱ አገግሞ በቶሎ ወደ ሜዳ ካልተመለሰ ብዙ ፉክክር ባለበት የቡድኑ ስብስብ ውስጥ ዳግም የተሻለ ሆኖ ለመታየት ነገሮች ቀላል ላይሆኑለት ይችላሉ።

👉 የተዳከመው ያሬድ ዘውድነህ

በተለያዩ ክለቦች በመሀል ተከላካይነት እና በመስመር ተከላካይነት ባለፉት ዓመታት ጥሩ ግልጋሎት ይሰጥ የነበረው ያሬድ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በድሬዳዋ ከተማ እያሳየ የሚገኘው እንቅስቃሴ በእጅጉ ጥያቄ የሚያስነሳበት ነው።

ከአካላዊ ዝግጁነት አንፃር በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ለመጫወት ከሚያስፈልገው መጠን እጅጉን ባነሰ የዝግጁነት ደረጃ ላይ የሚገኘው ተጫዋቹ ከፍጥነት እና አካላዊ ቅልጥፍና ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ስህተቶችን እየፈፀመ ይገኛል። ታድያ ተጫዋቹ በከፍተኛ ደረጃ እየተጫወተ ለመዝለቅ የሚፈፅማቸውን ስህተቶችን በአፋጣኝ አርሞ ራሱን አሻሽሎ በሁለተኛው ዙር መቅረብ ካልቻለ መጪዎቹ ጊዜያት በፈተና የተሞሉ ሊያደርግበት ይችላል። ቡድኑ በጉዳት ያጣቸው ተጨዋቾች ወደ ሜዳ ሲመለሱ እና ክፍተቱን ለማጠናከር ተጨማሪ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም ያሬድ በድጋሚ ከመጀመሪያ ዕቅድነት ውጪ እንዳይሆን ያሰጋዋል።

👉 ዕድሉን ያልተጠቀመው ጆርጅ ደስታ

የጀማል ጣሰውን ቅጣት ተከትሎ የመሰለፍ ዕድል ያገኘው ወጣቱ ግብ ጠባቂ ጆርጅ ደስታ አራት ጎሎችን በቅዱስ ጊዮርጊስ አስተናግዷል። በጉዳት እና ቅጣት የሳሳው ወልቂጤ በዓመቱ በአጠቃላይ የተቆጠረበትን ጎል ግማሽ በአንድ ጨዋታ ባስተናገደበት ዕለት ደካማ ቀን ካሳለፉ የቡድኑ ተጫዋቾች አንዱ ጆርጅ ደስታ ነው።

የወልቂጤ ከተማ 2ኛ ተመራጭ ግብ ጠባቂ የሆነው ጆርጅ ከዚህ ቀደም በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ መርሃግብር ወልቂጤ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሁለት አቻ በተለያየበት ጨዋታ እንዲሁ የጀማል ጣሰውን ጉዳት ተከትሎ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ቢሆን የመሰለፍ ዕድልን አግኝቶ የነበረ ሲሆን በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ከኢትዮጵያ መድን ጋር ያሳየውን ብቃት በጨዋታ ደቂቃዎች እጦት ያጣው ይመስላል። በጊዮርጊሱ ጨዋታ ያሳየው አቋምም ዳግም በመሰል ከባድ ጨዋታ ላይ ዕምነት አግኝቶ የመሰለፉን ነገር ጥያቄ ውስጥ የከተተ ሆኖ አልፏል።

👉 ሀብታሙ ገዛኸኝ ወዴት አለ ?

የአዲስ ግደይን መልቀቅ ተከትሎ የቡድኑ ዓይን እንደሚሆን ሲጠበቅ የነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝ የሚታይ ተፅዕኖ በቡድኑ ላይ መፍጠር ተስኖታል።

እንደ ቡድን እጅግ የተዳከመ የውድድር አጋማሽ ባሳለፈው የሲዳማ ቡድን ውስጥ ከአዲስ ግደይን ጥላ ተላቆ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ይበልጥ ራሱን እንደሚያሳይ ቢገመትም ተጫዋቹ እዚህ ግባ የሚባል አበርክቶን ለተቸገረው ቡድኑ እየሰጠ አይገኝም። እአንድ ግብ ብቻ ማስቆጠር የቻለው ሀብታሙ በሌሎቹ የቡድኑ ግቦች ላይም ከነበረው አበርክቶት መቀነስ በተጨማሪ ሜዳ ላይ እንደቀደሙት ዓመታት በእንቅስቃሴው የተጋጣሚ ተከላካዮችን ሲፈትን አይታይም።

ከአዲስ ግደይ በመቀጠል ሲዳማ ቡና በመልሶ ማጥቃት ለነበረው ስልነት ወሳኝ የነበረው ሀብታሙ ምንም እንኳን ዘንድሮ ቢቀዛቀዝም ተከታታይ ዕድሎችን ሲያገኝ ቆይቷል። ያም ቢሆን በተለይ በ12ኛው ሳምንት ቡድኑን ጅማን ሲገጥም ሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ አሰልጣኝ ገብረመድህን ቀይረው አስወጥተውታል። ይህም ሲዳማ አዲስ ከሚያስፈርማቸው አጥቂዎች ጋር መፎካከር ካልቻለ ቀዳሚ ተመራጭነቱን ሊያጣ እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ነበር። በቀጣዮቹ ጨዋታዎችም በአንዳች መንገድ እጅግ የወረደው በራስ መተማመኑን መልሶ ማግኘት እና ወደ ግብ አስቆጣሪነቱ መመለስ ካልቻለ ዓመቱ ለሀብታሙ ጥሩ የሚሆን አይመስልም።

👉 የሙጂብ ቃሲም መቀዛቀዝ

አስደናቂ የጎል ማስቆጠር አቋሙን በዚህ ዓመት ያሳየው ሙጂብ ቃሲም ባለፉት ጨዋታዎች ተቀዛቅዞ ታይቷል።

አስራ ሁለት ጎሎች ላይ ከደረሰ ወዲህ ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር የተሳነው ሙጂብ በአስደናቂ ግስጋሴ ላይ ከሚገኘው አቡበከር ናስር ጋር ያለው ልዩነት ወደ አምስት ጎል ከፍ ብሏል። እርግጥ ፋሲል ከነማ ከሌሎች ተጨዋቾቹ ግቦችን እያገኘ በውጤታማነቱ መቀጠሉ በሙጂብ ላይ ያለውን ትኩረት የቀነሰው ቢሆንም የግዙፉ አጥቂ ተፅዕኖ መውረድ ግን በጉልህ የሚታይ ጉዳይ ሆኗል።

ከሦስተኛው ሳምንት ጀምሮ በተከታታይ ሰባት ጨዋታዎች ላይ በስሙ ግብ እያስመዘገበ የቆየው ሙጂብ አሁን ደግሞ የመጨረሻውን ግብ ካስቆጠረ ሦስት ጨዋታዎች ሆነውታል። እርግጥ ነው የተጨዋቹ ውጤታማነት በተጋጣሚዎች ዘንድ የተለየ ትኩረት እንዲደረግበት ምክንያት መሆኑ ነገሮች ቀላል እንዳይሆኑለት ቢያደርግም እንደ ትልቅ አጥቂነቱ የግብ ማግኛ አማራጮችን አስፍቶ በአስፈሪነቱ መቀጠል ይጠበቅበታል።

👉 አብዱልከሪም መሐመድ እየተመለሰ ነው ?

የ2010 የሊጉ ኮከብ ተጫዋች ካለፈው ዓመት ወዲህ የአቋም መውረድ እየታየበት ብሎም በተደጋጋሚ ጨዋታዎች በተጠባባቂ ወንበር ላይ እያሳለፈ ይገኛል።

በጠንካራ የሥራ ባህሪው የሚታወቀው አብዱልከሪም በዚህ ዓመትም በአሰልጣኝ ማሒር ዴቪድስ ቀዳሚ ተመራጭ ሆኖ ዓመቱን ቢጀምርም በሜዳ ላይ የነበረው ብቃት በቀደመው ልክ ሳይሆን ቀርቷል። በዚህም መነሻነት ወጣቱን አማኑኤል ተርፉን ጭምር ዕድል እየሰጠ በታየው የቡድኑ የኋላ ክፍል ውስጥ የሚና መሸጋሸግ በማድረግ ፍሪምፖንግ ሜንሱ እና ደስታ ደሙን መጠቀም ከውብዱልከሪምን ከማሰለፍ የተሻለ የቡድኑ ዕቅድ ሆኖ እስከቅርብ ጨዋታዎች ይታይ ነበር።

ባለፉት ሁለት ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ግን አብዱልከሪም በግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ተካቶ ወደ ቀድሞ አቋሙ እየተመለሰ ስለመሆኑ ምልክት ሰጥቷል። ከፍ ባለ የማጥቃት ተሳትፎ የታጀበው የአብዱልከሪም ይህ ብቃት በቀጣይ ጨዋታዎች ላይም ተደግሞ ዳግም የአሰልጣኞቹን ዕምነት በቋሚነት ያስገኝለት እንደሆን በቀጣይ የሚጠበቅ ይሆናል።

👉ቡልቻ በመጨረሻም ጎል አስቆጥሯል

ዘንድሮ ወደ ሰበታ ከተማ ያመራው ቡልቻ ሹራ በበርካታ ጨዋታዎች የነበረው የጨዋታ ፍላጎት እና የጎል ዕድል የመፍጠር አቅም በጉልህ ሲታይ ቢቆይም እንደ መስመር አጥቂ ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ የማድረግ ጉዳይ ላይ ድክመቶች ተስተውለውበት ቆይቷል።

በዚህም መነሻነት የቀድሞው የአዳማ ከተማ አጥቂ ከመጀመሪያ ተመራጭነት ወርዶ በተጠባባቂነት ጨዋታዎችን ለመጀመር ተገዶ ነበር። ይሁን እና በ 12ኛው ሳምንት ጉዳት ያስተናገደው ፉዓድ ፈረጃን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን በዚህኛው ሳምንት ደግሞ ተቀዳሚ ተመራጭ ለመሆን በቅቷል። በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ልዩነት መፍጠር የሚችለው ፈጣኑ አጥቂ የቀደመ አስፈሪነቱን መልሶ የማግኘት ፍንጭን እያሳየ ግብ ማስቆጠር ብቻ ቀርቶት ቢቆይም በዚህኛው ሳምንት ግን ተሳክቶለት ተመልክተናል። ታታሪው ቡልቻ በ13ኛው ሳምንት ድንቅ የጨዋታ ቀን ሲያሳልፍ የፋሲልን ያለመሸነፍ ጉዞ የገታች ጎል ለማስቆጠርም በቅቷል። ተጨዋቹ ከግቧ በኋላ ደስታውን የገለፀበት መንገድም የነበረበትን እልህ እና ከአግቡነት ርቆ መቆየቱ የፈጠረበትን ስሜት የሚያሳይ ነበር።

👉 የአልሀሰን ካሉሻ የኤሌክትሪክ አቋም እየተመለሰ ይሆን ?
ጋናዊው የአጥቂ አማካይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በተቀላቀለበት 2010 ምንም እንኳ ቡድኑ ወደ ከፍተኛ ሊግ ቢወርድም በግሉ በብዙዎች ዓይን ውስጥ እንዲቀር ያደረገ ብቃቱን ማሳየት ችሎ ነበር ። በቀጣዩ ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርቶ ያልተሳካ ጊዜ ያሳለፈው አማካዩ ባለፈው ዓመትም ወደ መቐለ አምርቶ ገና ሁለት ጨዋታ እንዳደረገ ውድድሩ ተቋርጧል። መልካም አቋሙን ካሳየን በመቆየቱ የተነሳም ዳግመኛ ያንሰራራል የሚለው ዕምነት በብዙዎች ዘንድ አልነበረም።

ዘንድሮ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ያመራው አማካዩ በተጠባባቂነት ባመዘነ ሁኔታ ውድድሩን ቢጀምርም ቀስ በቀስ ሲሰለፍ ቆይቶ በቅርብ ጨዋታዎች ላይ በመደበኝነት እየተጫወተ ይገኛል። ባለፈው ሳምንት ከቡና ፣ በዚህ ሳምንት ደግሞ ከጅማ ጋር በተደረጉት ጨዋታዎች ላይ ያሳየው እንቅስቃሴም ‘የኤሌኬትሪኩ ካሉሻ እየተመለሰ ይሆን ?’ የሚያስብል ነው። ልዩ የቴክኒክ ችሎታ ባለቤት የሆነው ግራኙ ጋናዊ ከፍ ባለ በራስ መተማመን የግብ ዕሎችን ለመፍጠር እና በግሉ የተጋጣሚን ክፍተቶችን ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ወደ ራሱ እየተመለሰ መሆኑን የሚያመላክት ጊዜ ላይ ይገኛል። በቡናው ጨዋታ በእጅጉ ለግብ ተቃርቦ የተመለከትነው ተጫዋቹ በዚህ ሳምንት ቡድኑ አጥብቆ ይፈልግ የነበረውን ድል ያገኘባትን ጎል በስሙ ማስመዝገብ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ