“ግብ ማስቆጠር ላይ ያሉብኝን ክፍተቶች ለማሻሻል እየሰራሁ ነው” አህመድ ሁሴን

ከአንድ ዓመት በኃላ ወደ ጎል አስቆጣሪነቱ ዛሬ ከተመለሰው የወልቂጤው ግዙፍ አጥቂ አህመድ ሁሴን ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል።

በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ እስካሁን በተደረጉ አስራ አምሰተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ውስጥ በአንፃራዊነት ግልፅ የማግባት አጋጣሚ እንደ ወልቂጤው ግዙፉ አጥቂ አህመድ ሁሴን አግኝቶ ሳይጠቀም የቀረ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። በኮሮና ምክንያት በተሰረዘው የዓምናው የውድድር ዘመን ዓዲግራት ላይ ወልቂጤ ከወልዋሎ ሦስት አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ጎል ካስቆጠረ በኃላ አህመድ ሁሴን እና ጎል ለአንድ ዓመት ተራርቀው ነበር። የሚገርም ግጥጥሞሽ ሆኖ የዘንድሮውን የመጀመርያ ጎሉን በወርሀ የካቲት በአስራ አምስተኛው ሳምንት ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር ላይ ማስቆጠር መቻሉ ነው።

አህመድ ጎል መራቁን ተከትሎ ተጫዋቹ ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደነበረ ዛሬ ጅማ የማሸነፊያውን ጎል ካስቆጠረ በኃላ ደስታውን በእንባ ሲገልፅ ተመልክተነዋል። ሶከር ኢትዮጵያም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አህመድ ከጎል ስለራቀበት እና ሌሎች ጉዳዮችን አንስተንለት ያደረግነውን አጭር ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።

“ጎል መራቅ በጣም ከባድ ነው። ጫናው እንዲህ በቃላት የሚገለፅ አይደለም። ያው እኛ አገር አጥቂ ስትሆን ጎል ማስቆጠር አለብህ። ጎል ከአጥቂ ነው የሚጠበቀው። ጎል ሳታገባ ስትቀር ትጨነቃለህ። ዛሬ ከረጅም ጊዜ በኃላ ጎል አስቆጥያለው። ከጎል እርቄ ስለነበር ትንሽ ተጨንቄ ነበር ።ቡድናችንም ከውጤት ዕርቆ ነበር እና ጎል ሳስቆጥር ደስ ብሎኝ ነው ያለቀስኩት።

” ዓምና የካቲት ወር ነው የመጨረሻ ጎሌን ያስቆጠርኩት ዛሬ ደግሞ የዚህ ዓመት የመጀመርያ ጎሌን የካቲት ወር አስቆጥሬያለው። ያው እኔና የካቲት ወር የተለየ ግጥጥሞሽ አሉን ማለት ነው። ፈጣሪ ይመስገን ዓምና አምስት ጎሎች ነበሩኝ። ከዚህ በኃላም ከዚህ የተሻለ ጎል ለማስቆጠር አስባለሁ።

” አጋጣሚዎችን ለመጠቀም እና ግብ ለማግባት ያሉብኝን ክፍተቶች ላማሻሻል ጥረት አድርጌ እየሰራሁ ነው። ብዙ ጊዜ ለማግባት ከመጓጓት ነው ግቦችን የምስተው። ይህን ለማስተካከል ብዙ መስራት አለብኝ።

“በቀጣይ ፈጣሪ ካለ የተሻለ ነገር መፍጠር እፈልጋለሁ። ክለቤንም ራሴንም የሚጠቅም ነገር መስራት እፈልጋለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ