ሲዳማ ቡና ተጫዋች ማስፈረሙን ቀጥሏል

ቡድናቸውን እያጠናከሩ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች በዛሬው ዕለት የአጥቂ መስመር ተጫዋች ለማስፈረም መስማማታቸው ታውቋል።

የሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ የሆኑትን ገብረመድህን ኃይሌን በዋና አሠልጣኝነት የሾሙት ሲዳማ ቡናዎች ካሉበት አስጊ ደረጃ ለመሻሻል ዝውውሮችን እየፈፀሙ ይገኛሉ። ከቀናት በፊት ሦስት ወሳኝ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ የቀላቀለው ክለቡ በዛሬው ዕለት ደግሞ የአጥቂ መስመር ተጫዋቹን ያሬድ ከበደን ለማስፈረም ስምምነት ፈፅሟል።

መቐለ 70 እንድርታን ከከፍተኛ ሊግ ጀምሮ ሲያገለግል የነበረው የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ያሬድ ከወራት በፊት ለወልቂጤ ከተማ ለመጫወት መስማማቱ ሲነገር ነበር። ሆኖም ግን ዝውውሩ በስምምነት አለመገባደዱት ተከትሎ እስካሁን ያሬድ ያለ ክለብ ቆይቷል። በዛሬው ዕለትም የቀድሞ አሠልጣኙ ገብረመድህንን በመከተል መዳረሻውን ሲዳማ ማድረጉ ተነግሯል። የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳው ያሬድ ቡድኑን መቀላቀልም የሊጉን ዝቅተኛ ግብ አስቆጣሪ የአጥቂ መስመር ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ