ሪፖርት | በውዝግብ በተጠናቀቀው ጨዋታ ፋሲል ከነማ አሸናፊ ሆኗል

የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ የተሰጠው የፍፁም ቅጣት ምት በያሬድ ባዬ አማካይነት ወደ ግብነት ተለውጦ ፋሲልን ባለድል አድርጓል።

ሁለቱ ተጋጣሚዎች ከመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው ባደረጓቸው ለውጦች ፋሲል ከነማ አምሳሉ ጥላሁንን በሳሙኤል ዮሐንስ ምትክ የተጠቀመ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ባህሩ ነጋሽን በዓለም ብርሀኑ ምትክ አሰልፏል።

ትልቅ ግምት በተሰጠው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱ ተጋጣሚዎች ተጠባብቀው እና ራሳቸውን ከስህተት ጠብቀው ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል። በተሻለ ወደ ግብ ሲቀርቡ ባታዩባቸው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሁለቱም ጥሩ የሚባሉ የግብ ዕድሎችን ፈጥረው ነበር። 3ኛው ደቂቃ ላይ ከሱራፌል ዳኛቸው በተነሳ ኳስ ሽመክት ጉግሳ በቀኝ መስመር ገብቶ አደገኛ የግብ ዕድል መፍጠር ቢችልም ተቀባይ አላገኘም። ጊዮርጊሶችም ከሦስት ደቂቃ በኋላ በተመሳሳይ አስቻለው ታመነ ባስጀመረው ኳስ በቀኝ መስመር በመልሶ ማጥቃት ግብ ላይ ደርሰው የአቤል ያለው ሙከራ በሚኬል ሳማኬ ድኗል።

ፋሲሎች በጊዮርጊስ የግራ መስመር በኩል ያገኙ በነበረው ክፍተት ጊዮርጊሶችም በፈጣን የማጥቃት ሽግግር በመታገዝ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ግብ ፍለጋ ተንቀሳቅሰዋል። ሆኖም አፄዎቹ በ19ኛው እና 25ኛው ደቂቃ በሙጂብ ቃሲም ከሳጥን ውስጥ እንዲሁም በሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ውጪ ኢላማቸውን የጠበቁ ግን ደግሞ ክብደት የሌላቸው ሙከራዎችን ሲያደርጉ ፈረሰኞቹም በግራ መስመር አጥቂያቸው አማኑኤል ገብረሚካኤል አማካይነት ሁለት ሙከራዎች አድርገዋል ፤ የአማኑኤል ሁለተኛ ሙከራ የግቡን ቋሚ ታኮ የወጣ ነበር።

ጨዋታው 20ኛውን ደቂቃ ከተሻገረ በኋላ የጀመረው ካፊያ ግን የቡድኖቹን ጥንቃቄ ከፍ ሲያደርገው የማጥቃት እንቅስቃሲያቸው ደግሞ በተደጋጋሚ በሚቆራረጡ ቅብብሎች ሳቢያ ከስኬት እንዲርቅ ምክንያት ሆኗል። ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ሳጥኑ ይጥሉ የነበሩት ጊዮርጊሶች በተሻለ ሁኔታ አደጋ የሚፈጥሩ አጋጣሚዎችን ለማግኘት ቢቃረቡም የሳማኬ ጥንቃቄ ከሙከራ አግዷቸዋል። ከሱራፌል ረጅም ኳሶች እና በመስመር በኩል ከሚከፍቷቸው መልሶ ማጥቃቶች ግብ ላይ ለመድረስ ይሞክሩ የነበሩት ፋሲሎችም ጥረታቸው ሳይሰምር አጋማሹ ተገባዷል። ዕረፍት ሊወጡ ሲቃረቡም የጊዮርጊሱ አቤል ያለው ባስተናገደው ጉዳት በአዲስ ግደይ ለመቀየር ተገዷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ቀዝቃዛ አጀማመር ያደረገ ነበር። በአመዛኙ በጊዮርጊስ ሜዳ ላይ በነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ፋሲሎች ያልተመጠኑ የመጨረሻ ኳሶቻቸው የግብ ዕድል እንዳይፈጥሩ ሲያደርጋቸው ከተጋጣሚው የግብ ክልል የራቀው የቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት ጥረትም ፋሲልን ለመፈተን አላስቻለውም። የአጋማሹ የመጀመሪያ ጠንካራ ሙከራም የታየው 70ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ዳስታ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በባህሩ ነጋሽ ሲሚለስ ነበር። ጊዮርጊሶችም በአንድ ደቂቃ ልዩነት ወደ ግብ ደርሰው የጌታነህ ከበደ ጠንካራ የሳጥን ውጪ ሙከራ በሳማኬ ጥረት ለጥቂት ግብ ከመሆን ድኗል።

ጨዋታው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አጥቶት የነበረውን የግብ ሙከራዎች ትዕንት ማግኘት ችሏል። 80ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ በኩል ከእንየው ካሳሁን በተሻማ ኳስ ጥሩ ዕድል አግኝተው መጠቀም ባልቻሉት ፋሲሎች በኩል 82ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ መለዮ ከሱራፌል የቅጣት ምት መልስ ያገኘውን ኳስ ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። እጅግ ለግብ በቀረበው የጨዋታው ሙከራ ከሩቢን ንጋላንዴ ቅያሪ በኋላ የተሻለ በሳጥኑ ዙሪያ የቆዩት ጊዮርጊሶች በፈጠሩት ዕድል 85ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ አዲስ ግደይ ሞክሮ በእንየው ካሱን ተጨርፎ በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል።

የቡድኖቹ ፍልሚያ ያለ ግብ ለመጠናቀቅ በተቃረበበት ሰዓት የጨዋታውን አጠቃላይ መንፈስ እና ውጤት የቀየረ ክስተት ተፈጥሯል። ጭማሪ ደቂቃ ላይ የጊዮርጊሱ ተከላካይ አስቻለው ታመነ ሙጂብ ቃሲምን ቀይሮ ወደ ሜዳ ከገባው ፍቃዱ ዓለሙ ጋር የነበረውን ንክኪ ተከትሎ የዕለቱ አርቢትር ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ለፋሲል ከነማ ፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል። የቡድኑ አንበል ያሬድ ባየህም አጋጣሚውን በተረጋጋ ሁኔታ ወደ ግብነት ለውጦ ለቡድኑ እጅግ አስፈላጊ የነበረውን ድል አስገኝቷል። ይህን የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔ ተከትሎም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም ጭምር በእለቱ አርቢትር ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ ተስተውሏል።

ውጤቱን ተከትሎ መሪው ፋሲል ከነማ ከቅርብ ተፎካካሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስምንት ማስፋት ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ