ሪፖርት | ጅማ በአዳማ ላይ ወሳኝ ድል አስመዝግቧል

በሊጉ ግርጌ የሚገኙትን ሁለት ቡድኖች ያገናኘው ጨዋታ በጅማ አባ ጅፋር 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አዳማ ከተማ በኢትዮጵያ ቡና ከተራታበት ጨዋታ ባደረጋቸው ለውጦች በታሪክ ጌትነት ፣ ደስታ ጊቻሞ ፣ ትዕግስቱ አበራ ፣ ደሳለኝ ደባሽ እና ክለቡን በለቀቀው ሙጃይድ መሀመድ ቦታ ዳንኤል ተሾመ ፣ አሚኑ ነስሩ ፣ ኤልያስ አህመድ ፣ ጀሚል ያዕቆብ እና ብሩክ መንገሻ ተጠቅሟል። በአንፃሩ ጅማዎች ከሆሳዕናው ጨዋታ ሙሉቀን ታሪኩን በአዲስ ፈራሚው አማኑኤል ተሾመ ለውጠዋል።

ተመጣጣኝ ፉክክርን ያስመለከተን የመጀመሪያ አጋማሽ በሙከራ ረገድ ዕምብዛም ነበር። በአዲስ መልኩ እንደተዋቀረ ቡድን ሳይሆን የተሻለ የኳስ ቁጥጥርን በመያዝ ያሳለፉት አዳማዎች የግብ ዕድሎችን መፍጠር ላይ ስኬታማ አልነበሩም። ጨዋታው እንደጀመረ በግራ መስመር በጀሚል ያዕቆብ እንዲሁም 20ኛው ደቂቃ ላይ በብሩክ መንገሻ ከሳጥን ውጪ ካደረጉት ሙከራ ውጪም ቅብብሎቻቸው በጅማ ሳጥን ውስጥ ደርሰው አደጋ ሲፈጥሩ አልታዩም።

ጅማዎችም ቢሆኑ የተጋጣሚያቸው የኳስ ቁጥጥር ከሁለተኛው የሜዳ ክፍል እንዳያልፍ ማድረግ ያልከበዳቸው ቢሆንም ከሚቋረጡ ኳሶች ወደ ፊት ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት ተደጋጋሚ የግብ አጋጣሚዎችን አላስገኘላቸውም። ሆኖም 14ኛው ደቂቃ ላይ ከአዳማዎች የቅብብል ስህተት ጥሩ አጋጣሚ አግኝቶ ያልተጠቀመው ሳዲቅ ሴቾ 29ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ደረሰ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ቀለል ባለ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ ጅማን ከዕረፍት በፊት መሪ ማድረግ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ አዳማዎች ሌላኛው ፈራሚያቸው ኤልያስ ማሞን ወደ ሜዳ በማስገባት ጭምር በኳስ ቁጥጥር የበላይነቱ ሲገፉበት በተሻለ ሁኔታ በጅማ ሳጥን ውስጥ መገኘትም ጀምረዋል። በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በተሰጠ ሁለተኛ ቅጣት ምትም 52ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ ማቲያስ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ጅማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ተመሳሳይ ዕድል አግኝተው ያልተጠቀሙበት ሲሆን በሊጉ ላይም የእዮብ ግብ በ2009 የውድድር ዘመን ንግድ ባንኩ ፒተር ኑዋዲኬ ኤሌክትሪክ ላይ ካስቆጠረው ጎል በኋላ የተመዘገበ ነበር።

አዳማዎች 61ኛው ደቂቃ ላይም ሌላ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው አሚን ነስሩ ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ሲመለስ ከተሰጠው የማዕዘን ምት ክፍት ኳስ አግኝቶ የነበረው ኤልያስ አህመድ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጅማ አባ ጅፋሮች በተቃራኒው ኳስ ይዘው ከራሳቸው ሜዳ መውጣት ከብዷቸው ሲታዩ አዲሱን የአሚኑ ነስሩ እና እዮብ ማቲያስ የመሀል ተከላካይ ጥምረት ለመረበሽ ሳይችሉ ቆይተዋል። 

ሆኖም 85ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ያገኙትን የቅጣት ምት አማኑኤል ተሾመ ሲያሻማ ንጋቱ ገብረሥላሴ በግንባሩ ሲገጭ በቃሉ ገነነ ጨርፏት ወሳኟ ጎል ተቆጥራለች። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በራሳቸው የግብ ክልል ሆነው በመከላከልም ነጥባቸውን 10 ያደረሱበትን ድል አስመዝግበዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ