ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ባህር ዳር ከተማ

የአስራ አራተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ መርሐ-ግብር የሆነውን ጨዋታ እንዲህ ተመልክተነዋል።

በደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ላይ ካሉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሲዳማ ቡና ከአራት የጨዋታ ሳምንታት በፊት ወልቂጤ ላይ ያገኘውን ሦስት ነጥብ ዳግም ለማሳካት እንዲሁም ከወራጅ ቀጠናው የመውጣትን ሀሳብ ሰንቆ ነገ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታል። ድል ካደረጉ አራት ጨዋታዎች ያለፋቸው ባህር ዳሮች በበኩላቸው በመቀመጫ ከተማቸው የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት እና ከመሪዎቹ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ተዘጋጅተው ለጨዋታው እንደሚቀርቡ ይገመታል።

አዲስ አሠልጣኝ በመሾም ካሉበት አስጊ ቀጠና ለመውጣት እየጣሩ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ውድድር ያሳዩትን ደካማ ብቃት ማሻሻል አለባቸው። በተለይም ቡድኑ ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል በሚገባበት ጊዜ የሚያጥረውን የማጥቃት ሀሳብ ማስተካከል ይኖርበታል። ከምንም በላይ ደግሞ ሁነኛ እና አይምሬ የአጥቂ አማራጭ አለመያዙ የፊት መስመሩ አስፈሪ እንዳይሆን አድርጎታል። ከዚህ መነሻነት በነገው ጨዋታ የስልነት ችግር አደጋ ውስጥ እንዳይከተው ያሰጋል።

በሊጉ አነስተኛ ጎል (7) ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረው ሲዳማ በነገው ጨዋታ ወደ ቡድኑ የቀላቀላቸውን አዳዲስ ተጫዋቾች መጠቀም መቻሉ መልካም ዜና ይሆንለታል። ከአራቱ ተጫዋቾች ውስጥ ከሦስቱ ጋር አሠልጣኙ ከዚህ ቀደም መስራታቸው ደግሞ ስራቸውን እንደሚያቀልላቸው ይገመታል። ከምንም በላይ ደግሞ በፈጠራ አቅሙ ተዳክሞ የነበረው ቡድኑ አዲስ ያስፈረመውን ዮናስ ከዳዊት ተፈራ ጋር በመሐል ሜዳው የሚያጣምር ከሆነ የፈጠራ አቅሙ እንደሚሻሻል ይታሰባል። ከዚህ መነሻነትም የሲዳማ አጥቂዎች ባህር ዳሮች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የሚያስችላቸውን ኳሶችን ከመሐል ሜዳው ሊያገኙ ይችላሉ።

ሲዳማ ቡና አዲስ ያስፈረማቸው ሽመልስ ተገኝ ፣ መሐሪ መና ፣ ዮናስ ገረመው እና ያሬድ ከበደ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆኑለት ጉዳት ላይ የሰነበተው ይገዙ ቦጋለ ልምምድ መጀመር ለቡድኑ መልካም ዜና ሊሆን የሚችል ነው። ከዚህ ውጪ ፈቱዲን ጀማል በቀይ ካርድ ቅጣት ዮሴፍ ዮሐንስ ደግሞ ቀዶ ጥገና በማድረጉ እንዲሁም ጉዳት ያስተናገደው ማማዱ ሲዲቤ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነውበታል።

በመቀመጫ ከተማቸው ሁለተኛ ጨዋታቸውን በነገው ዕለት የሚያከናውኑት ባህር ዳር ከተማዎች ከፍተኛ የወጥነት ችግር ኖሮባቸው የመጀመሪያውን ዙር አገባደዋል። ነጥብ በጣለባቸው ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ደግሞ የኋላ እና የፊት መስመሩ ላይ መጠነኛ ችግር እንዳለም አስመልክቷል። በ11ኛ ሳምንት በተደረገው እና ከጅማ ጋር 2-2 በተለያየው ጨዋታ ቡድኑ የኋላ መስመሩ የመዋቅር ክፍተቶችን ሲያስመለክት ነበር። በ12ኛው ሳምንት በተደረገው የወላይታ ድቻ ጨዋታ ደግሞ የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ሰብሮ ስል ሙከራዎችን ማድረግ ተስኖት ነበር። ከዚህ መነሻነት እነዚህን የቅርብ ጊዜ ስህተቶች ካላረመ በነገው ጨዋታ ሊጎዳ ይችላል።

ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረግ ፈጣን ሽግግሮች የተጋጣሚን የግብ ክልል መጎብኘት የሚያዘወትረው ቡድኑ ከድቻው ጨዋታ የወገብ በላይ ስህተቶቹ ታርሞ እንደ ወትሮ በነገው ጨዋታ የሚቀርብ ከሆነ ለተጋጣሚው ቡድን አደጋ ነው። በተለይም ፍጥነቱን ተጠቅሞ በተጋጣሚ ቡድን አማካይ እና ተከላካይ መካከል ያለውን ቦታ ለመጠቀም በሚጥረው አልፎም ከተከላካዮች ጀርባ ለመሮጥ የማይቦዝነው ፍፁም ዓለሙ ለቡድኑ ቁልፍ ሰው እንደሚሆን ይገመታል።

ባህር ዳር ከተማዎች በነገው ጨዋታ የጡንቻ ጉዳት ካስተናገደው አቤል ውዱ ውጪ የሚያጡት ተጫዋች እንደማይኖር ተጠቁሟል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሦስት የሊግ ጨዋታዎች ሲገናኙ አንዱን አቻ ተለያይተው ሁለቱን ባህር ዳር ከተማ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ችሏል። በጨዋታዎቹ ባህር ዳር አምስት እንዲሁም ሲዳማ ሁለት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

ሽመልስ ተገኝ – ጊት ጋትኮች – ሰንደይ ሙቱኩ – ግሩም አሰፋ

ዳዊት ተፈራ – ብርሀኑ አሻሞ – ዮናስ ገረመው

ተመስገን በጅሮንድ –ያሬድ ከበደ – አዲሱ አቱላ

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ሀሪሰን ሄሱ

ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ሳምሶን ጥላሁን

ሳላምላክ ተገኝ – ፍፁም ዓለሙ – ግርማ ዲሳሳ

ባዬ ገዛኸኝ


© ሶከር ኢትዮጵያ