ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የፀጋነሽ ወራና የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ድሬዳዋን ባለ ድል አድርጓል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አስራ አራተኛ ሳምንት ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ እና አዳማ ከተማ መሐል ተደርጎ ድሬዳዋ ከተማን 1ለ0 አሸናፊ ሆኗል፡፡

የድሬዳዋ ከተማዎች የበላይነት ሚዛን ደፍቶ በተስተዋለበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም የመስመር ኮሪደሮች ወደ ሳጥን በሚደረጉ ተሻጋሪ ኳሶች ወደ አዳማ የግብ ለመድረስ ብዙም ሳይቸገሩ አጨዋወታቸውን በአግባቡ መተግበር ችለዋል፡፡ በዚህም የጨዋታ መንገድ ገና ጨዋታው ተጀምሮ አንድ ደቂቃ ብቻ እንደተቆጠረ በቀኝ በኩል ኳስን ወደ ግብ ክልል ፀጋነሽ ወራና ይዛ ስትገባ አዳማ ከተማን በቅርቡ ከመቐለ የተቀላቀለችው ሰላማዊት ላዕከ በተጫዋቿ ላይ ጥፋት በመስራቷ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሷ ፀጋነሽ ወራና ከመረብ አሳርፋ ድሬዳዋ ከተማን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡

የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ አዳማ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢጥሩም በአጥቂ ክፍል የተሰለፉ ተጫዋቾች መረጋጋት የተሳናቸው በመሆኑ ወደ ግብ ክልል አካባቢ ሲደርሱ ኳሶቻቸው ሲባክኑ ታይቷል፡፡ በተለይ አጥቂዎቹ ምርቃት ፈለቀ እና ሰርካዲስ ጉታ ኳስን ይዘው ለቡድን ጓደኞቻቸው ከማቀበል ይልቅ ጥቅጥቅ ባለ መከላከል ውስጥ በግላቸው የያዙት ኳስ ተጫዋቾችን ለማለፍ ጥረት ሲያደርጉ በተደጋጋሚ ይነጠቁ ስለነበር ቡድኑን ዋጋ ያስከፈለ እንደነበር መታዘብ ይቻላል፡፡ አልፊያ ጃርሶ ከቅጣት ምት ሞክራ በግብ ጠባቂ የተመለሰባት አጋጣሚ ብቸኛ እና የጠራች የአዳማ ከተማ ሙከራ ነበረች፡፡ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች ከቆመ ኳስ በተደጋጋሚ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራን በፀጋነሽ ወራና አማካኝነት ሲያደርግ የተመለከትን ሲሆን ወደ ጎልነት ሊለወጡ ግን አልቻሉም፡፡

ከእረፍት መልስ ከጨዋታው ይልቅ አጨቃጫቂ የዳኝነት ውሳኔዎች በተደጋጋሚ መመልከት የቻልን ሲሆን አዳማዎች ምንም እንኳን በሁለተኛው አጋማሽ ተረጋግተው ቢመለሱም አሁንም እንደ ቡድን ከመጫወት ግላዊነት ላይ በይበልጥ ተሳትፎ ማድረጋቸው ጥቂት የሚባሉ ዕድሎቻቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ አላስቻላቸውም፡፡ በመስመር አደገኛ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው ታደለች አብርሀም ብረት የመለሰባት እና ፀጋነሽ ወራና ከርቀት በሞከረቻት ሙከራ አሁንም የአዳማን የግብ ክልል ሲፈትኑ ተስተውሏል፡፡

ከፉክክር ይልቅ የተቀዛቀዘ ሁለተኛ አጋማሽ ባየንበት ቀሪ 30 ደቂቃዎች በተደጋጋሚ የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ በዕለቱ ዳኞች ላይ በሚያሳየው ድርጊት የዕለቱ ዋና ዳኛ ማርታ መለሰ ማስጠንቀቂያ ካርድ የሰጥችው ሲሆን በዚህም መነሻነት 64ኛው ደቂቃ በዳኛዋ ላይ አዳማ ከተማዎች የቴክኒክ ክስ አስመዝግበዋል፡፡

በጭማሪ ደቂቃ የአዳማ ከተማዋ አጥቂ ምርቃት ፈለቀ ከድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች ጋር ተጋጭታ ጉዳት የገጠማት ሲሆን በሜዳ ታቅፋ ለመውጣት ተገዳለች። ተጫዋቿ የገጠማት ጉዳት በፊቷ አካባቢ ሲሆን ጉዳቱ ጠንከር ያለ ባለመሆኑ ወደ ሆስፒታል ሳታመራ ቀርታለች፡፡

በጭቅጭቅ የተሞላው ሁለተኛው አጋማሽ ምንም የተለየ ነገር ሳያስመለክተን በድሬዳዋ 1ለ0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ፀጋነሽ ወራና የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተመርጣለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ