ሀዲያ ሆሳዕና ወሳኙን አጥቂ አያገኝም

እንዳጀማመሩ ጉዞው ያላማረለት ሀዲያ ሆሳዕና ወሳኙን አጥቂ በቀጣይ ጨዋታ የማያገኝ ይሆናል።

በሀዲያ ሆሳዕና በዘንድሮው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ አራት ጎል በማስቆጠር ቡድኑን ውጤታማ በማድረግ አቅሙን እያሳየ የቆየው ሳሊፉ ፎፎና ከዚህ በኃላ በሚኖሩ ጨዋታዎች ለሀዲያ ሆሳዕና አገልግሎት እንደማይሰጥ ታውቋል።

አይቮሪኮስታዊው የፊት መስመር ተጫዋች ሳሊፉ ፎፋና ከጅማ ውድድር መጠናቀቅ በኃላ ወደ ሀገሩ አቅንቶ እስካሁን አልተመለሰም። ምንም እንኳን ኮንትራቱ ባለፈው ወር የተጠናቀቀ ቢሆንም ክለቡ ውሉን ለማራዘም ከፍተኛ ፍላጎት አሳይቶ ቆይቷል። ሆኖም ተጫዋቹ ባጋጠመው ቤተሰባዊ ጉዳይ ምክንያት ዳግመኛ መምጣት ባለመቻሉ ሳይሳካ ቀርቷል።

ምናልባት አሁን ያለው ግላዊ ችግር የሚፈታ ከሆነ በቀጣይ ድሬዳዋ ላይ ለሚካሄዱ ጨዋታዎች የመድረስ ተስፋ ሊኖር እንደሚችል ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ