ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ድሬዳዋ ከተማ

የነገ ከሰዓቱን ጨዋታ የተመለከትንበት ዳሰሳችን እንዲህ ይነበባል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ ወሳኝ የነበረው ጨዋታ ከእጁ ከወጣ በኋላ ከመሪው በስምንት ነጥቦች ርቆ ለነገው ጨዋታ ደርሷል። ከዋንጫ ፉክክሩ ከዚህ በላይ መራቅ የሌለበት በመሆኑም በተለየ ትኩረት ጨዋታውን እንደሚከውን ይጠበቃል። በአሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ ስር ሁለተኛ የአቻ ውጤት የያዘው ድሬዳዋ ከተማም በፊናው ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ እና በአንድ ደረጃ ብቻ ከፍ ብሎ መገኘቱ ውጤቱን አጥብቆ እንዲፈልገው የሚያደርገው ነው።

በሁለት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ማስቆጠር ችሎ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በፋሲሉ ጨዋታ የማጥቃት አማራጮቹ ቀንሰው ታይተዋል። እርግጥ ነው የነገው ጨዋታ ከተጋጣሚው የኋላ ክፍል ድክመት አንፃር የተሻለ ክፍተት የሚያስገኝለት ቢሆንም በፋሲሉ ጨዋታ በቅያሪ እና በሽግሽግ ሦስት ተጨዋቾችን (አቤል እንዳለ ፣ የአብስራ ተስፋዬ እና ሮቢን ንጋላንዴ) የጨዋታ አቀጣጣይነት ሚና ሲሰጥ መታየቱ አሁንም የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር አንፃር ያለበትን ጥያቄ አሳይቶ ያለፈ ጉዳይ ነበር። ይህን ችግር ለመፍታት የጌታነህ ከበደ በጥልቀት ተመልሶ ቅብብሎችን መከወን እንደ አማራጭ ቢታይም ቡድኑ ፊት ላይ ስልነት እንዲጎለው ሲያደርግ ይታያል።

ነገ ድሬዳዋ ጥብቅ መከላከልን ከመረጠ ቡድኑ በዚህ ረገድ ሊቸገር የሚችል ሲሆን በተሻለ መልኩ የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ በአቋቋም ደረጃ ለግብ ቀርበው እንዲንቀሳቀሱ ማድርግ እና ተቀዛቅዞ የታየውን የመስመር ተከላካዮቹን የማጥቃት ተሳትፎ አሻሽሎ መቅረብ ይጠበቅበታል። ከዛ ውጪ አሁንም ከስህተት መፅዳት ያልቻለው እና በግብ ጠባቂ ቦታ ላይም ለውጥ ለማድረግ የተገደደው የቡድኑ የኋላ ክፍል ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች መረቡን አለማስደፈር ተስኖት መታየቱ ሌላኛው የአሰልጣኝ ማሂር ዴቪድስ ቡድን ደካማ ጎን ከነገው ጨዋታ በፊት ስጋት ላይ የሚጥለው ጉዳይ ነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በግል ጉዳይ ከማይኖረው ፍሪምፖንግ ሜንሱ በተጨማሪ ባለፈው ጨዋታ ጉዳት ገጥሞት ለመቀየር የተገደደው አቤል ያለውን ግልጋሎት በነገው ጨዋታ አያገኝም። የእሱን ቦታ ተክቶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ የሚጠበቀው አዲስ ግደይም እጅግ በተዳከመ የእስካሁኑ የፈረሰኞቹ ቤት ቆይታው ብቸኛውን ጎሉን በመጀመሪያው ዙር የድሬዳዋ ጨዋታ ላይ ማስቆጠሩ ዳግም በብርቱካናማዎቹ ላይ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ይነቃቃል ወይ የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ይሆናል።

አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በተለይም ወደ ፊት በመድረሱ በኩል መሻሻል እያሳየ እንደሆነ ማመናቸውን የተናገሩለት ድሬዳዋ ከተማ ከመጨረሻው የሰበታ ጨዋታ አንፃር ነገ ከበድ ያለ ፈተና ይጠብቀዋል። ከሰበታ ጋር አሰልጣኙ የተጋጣሚያቸውን አጨዋወት ከግምት ያስጋባ ግብረ መልስ ለመስጠት በማሰብ የጨዋታ ዕቅዳቸውን መቅርፃቸው ነገም ተመሳሳይ ነገር እንድንጠብቅ ያደርገናል። በመሆኑም የተጋጣሚው ጠንካራ ጎን የሆኑት ሁለቱ መስመሮችን በመዝጋት ላይ ትኩረት የሚያደርግ እንደ ሰበታውም ጨዋታ በቶሎ ከራሱ ሜዳ በመልሶ ማጥቃት ለመውጣት የሚሞክር ዓይነት ቡድን በብርቱካናማዎቹ በኩል ይጠበቃል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ቡድኑ በዋነኝነት አስተማማኝ ያልሆነው የኋላ ክፍሉን አጠናክሮ መቅረብ ትልቁ ፈተናው ይሆናል። በአደረጃጀት እና በግለሰባዊ ስህተቶች ሲከፈት የሚታየው የተከላካይ መስመሩን ከማጠናከር አንፃርም አዲስ ፈራሚ ተጫዋቾቹን እንደአስፈላጊነቱ ወደ ሜዳ ሊያስገባ እንደሚችል ይጠበቃል። በማጥቃቱም ረገድ ድሬ በዋናነት ወደ ግራ ባደላ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ለመግባት ጥረት ሲያደርግ ታየ እንጂ ፊት ላይ ያለው ደካማ የቅብብል ስኬቱ የመጨረሻ የግብ ዕድል ከመፍጠር ሲያርቀው መታየቱ ሌላኛው ደካማ ጎኑ ነው። ከተጋጣሚው የቦታው ጥንካሬ አንፃርም የመስመር ተከላካዮችን ለማጥቃት ግብዓት ማድረግ ሌላ አደጋ ስለሚኖረው በምን መልኩ ይህን ችግሩን ያስተካክላል የሚለው ነጥብ ተጠባቂ ይሆናል።

ድሬዳዋ ከተማ በረከት ሳሙኤል ዳግም ወደ ልምምድ የተመለሰለት መሆኑ መልካም ዜናው ሲሆን አራት የሚደርሱ ተጨዋቾቹ ውል ከማራዘም ድርድር ጋር በተያያዘ ከቡድኑ ጋር ላይኖሩ ይችላሉ። ከዚህ ውጪ አዲስ ፈራሚዎቹ ዐወት ገብረሚካኤል ፣ ሄኖክ ገምቴሳ እና ወንደወሰን አሸናፊ ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸውን ሰምተናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በፕሪምየር ሊጉ 17 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 12 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ 3 ጊዜ ድል ቀንቶታል፡፡ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ጊዮርጊስ 31 ጎሎችን ሲያስቆጥር ድሬዳዋ 13 ጎሎች አሉት።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ባህሩ ነጋሽ

ሄኖክ አዱኛ – አስቻለው ታመነ – ደስታ ደሙ– አብዱልከሪም መሀመድ

የአብስራ ተስፋዬ – ናትናኤል ዘለቀ

አዲስ ግደይ – አቤል እንዳለ – አማኑኤል ገብረሚካኤል

ጌታነህ ከበደ

ድሬዳዋ ከተማ (4-3-3)

ፍሬው ጌታሁን

ዐወት ገብረሚካኤል – ያሬድ ዘውድነህ – ፍሬዘር ካሳ – ሄኖክ ኢሳይያስ

አስቻለው ግርማ – ዳንኤል ደምሴ – ሱራፌል ጌታቸው

ጁኒያስ ናንጄቦ – ሙኸዲን ሙሳ – ኢታሙና ኬይሙኒ


© ሶከር ኢትዮጵያ