የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 0-1 ፋሲል ከነማ

ተጠባቂው ጨዋታ በፋሲል 1-0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለጨዋታው

የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ትንሽ ኃይል የቀላቀለ ጨዋታ ነበር። ቢሆንም ግን የመውጫ ቦታዎች ነበሩ። ግን ኳሶች ሲበላሹ እና ሲቋረጡ ያንን ክፍተት እያገኙ የተወሰኑ ኳሶች ሞክረውብናል። በዕረፍት ሂደቱን ሳንለቅ በዛ ክፍተት እንዳይጠቀሙ ክፍተቶችን እየዘጋን የጎል ዕድል መፍጠር ነበር። ያው ከዕረፍት በኋላ ብዙ የተጨዋች ቁጥር እነሱ ሜዳ ላይ ነበር። ወደ ጎል አካባቢ ቀርበናል ግን በመጨረሻ ላይ የነበሩ ውሳኔዎች ላይ ስህተት ነበር። ያ ነበር የእኛ ድክመት።

ስለዋንጫ ፉክክሩ

ገና እንግዲህ ሁለተኛው ዙር መጀመሩ ነው። ይሄ ሁለተኛ ጨዋታችን ነው። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ብዙ ጨዋታዎች አሉ። አሁንም ቢሆን ለቻምፒዮንነት ለመጫወት ዕድሉ አለን።

ሊሻሻሉ ስለሚገቡ ችግሮች

ተከታታይ ባይሆንም ጫና ሲፈጠር ኋላ ላይ የምንሰራቸውን ስህተቶች መቀነስ ፤ የራሳችን ስህተቶች ማለት ነው። ምክንያቱም ተጋጣሚ ያን ኳስ ካገኘ በኋላ ነው የሚጠቀምበት። ሌላ እንግዲህ ወደ ተጋጣሚ ጎል ስንቀርብ የቁጥር ክምችት ሲገጥመን ያን የምንቀርፍበትን መንገድ ነው ማስተካከል የሚኖርብን።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለቻምፒዮንነት ማሰብ ስለመጀመራቸው

አዎ ማለት እችላለሁ። ምክንያቱም ከእኛ ጋር እኩል የሚወዳደሩትን በዚህ ነጥብ ርቀት 8 ፣ 9 እና 10 መራቅ ቀላል ነገር አይደለም። በቡድኑ ሥነ-ልቦና ላይ የሚፈጥረው ጥንካሬ ትልቅ ነው። ከሁሉም በላይ ሁለተኛውን ዙር ስንጀምር ከጠንካራዎቹ ነው የጀመርነው ፤ ከቅዱስ ጊዮርጊስም ከኢትዮጵያ ቡናም ጋር። እነዚህን ተፎካካሪዎችን አሸንፈን መውጣቱ ከሁለቱም ስድስት ነጥብ ማግኘት አጠቃላይ የቡድናችንን ጥንካሬ እና የሥነ-ልቦና ከፍታን ያሳያል እና በጣም ጥሩ ቀን ነው ብዬ አስባለሁ።

ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጥንቃቄ ስለማዘንበሉ

ትክክል ፤ ሀይ ፕሬሲንግ 90 ደቂቃ አትችልም። እና የመጀመሪያው አጋማሽ የተጫወትነው ሀይ ፕሬሲንግ የተጨዋቾችን ጉልበት ያወርዳል። በዛ ሰዓት ግን መጠቀም የሚገባንን ቢያንስ ከሦስት ያላነሱ ዕድሎች መጠቀም ነበረብን። አልተቻለም ፤ 1-0 ይዘን ወጥተናል። እና የመጀመሪያው 45 ላይ ያወጡት ጉልበት ሁለተኛው ላይ ለመድገም እንዳዳገታቸው ያስታውቃል። ያም ቢሆን የኢትዮጵያ ቡናን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ የነበረውን የኳስ ቁጥጥር ለማጥፋትም ሆነ ዘልቀው እንዳይገቡ እንደቡድን ስናደርግ የነበረው መልካም ነገር ነው። እና ውጤቱን አስጠብቀን መሄዳችን ትልቅ ነገር ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ