ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የአስራ አምስተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየራ ሊግ የመጨረሻ መርሐ-ግብር የሆነውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከአራት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ሲዳማ ቡና ላይ ድል ተቀዳጅተው ለዚህኛው ግጥሚያ እየተዘጋጁ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች ከበርካታ ጊዜያት በኋላ ያገኙትን የአሸናፊነት መንፈስ ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ። በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ጎል አስተናግደው በወላይታ ዲቻ የተረቱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው አሁንም በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ እንዳሉ ለማሳየት እና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ድልን ተቀዳሚ ዓላማ አድርገው ለጨዋታው ይቀርባሉ።

በ14ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ከመመራት ተነስተው ድል ያገኙት የአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ተጫዋቾች በጨዋታው የሁለተኛ አጋማሽ ያሳዩት ብቃት ድንቅ ነበር። ከምንም በላይ በጫናዎች ውስጥ ሆነው የግብ ማስቆጠሪያ አማራጮችን ለመፈለግ ሲታትሩበት የነበረበት መንገድ መልካም ነበር። በተለይም ግን ቡድኑ የሜዳውን የጎንዮሽ ስፋት በመስመር አጥቂዎቹ እና ተከላካዮቹ ( በተለይ ወሰኑ፣ ሚኪያስ እና አህመድ) እየለጠጠ የተጋጣሚን የመከላከል አደረጃጀት እንዲዘረዘር ሲያደርግ ለቡድኑ ጠቀሜታን በሚያስገኝ መልኩ ነበር። ይህ አጨዋወቱም ደግሞ ነገ እጅግ የሚያስፈልገው ይመስላል። በተለይ እጅግ ጠንካራውን የሀዲያን የተከላካይ መስመር ሰብሮ ለመግባት ጊዜያቸውን የጠበቁ ፈጣን የመስመር ላይ ሽግግሮች ወሳኝ ናቸው። ከዚህ መነሻነት ቡድኑ በዚህ አጨዋወት ራሱን አዘጋጅቶ ወደ ሜዳ ሊገባ እንደሚችል ይታሰባል።

የኋላ መስመሩ አሁንም ወጥ ብቃት አላስመለክት ያለው ቡድኑ ነገ ከሽንፈት የተመለሰውን ሀዲያ ለመቆጣጠር በከፍተኛ ብቃቱ ላይ መገኘት የግድ ይለዋል። በዋናነት በዳዋ ሆቴሳ የሚመራው የሀዲያ የፊት መስመር በተለያዩ የማጥቂያ አማራጮች ግብ ለማስቆጠር የማይሰንፍ ስለሆነ በከፍተኛ የትኩረት ደረጃ ላይ መገኘት ይሻል።

ባህር ዳር ከተማ በነገውም ጨዋታ የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ አቤል ውዱን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኝም።

በዘንድሮ የውድድር ዘመን ቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ የቀረበው ሀዲያ ለተጋጣሚ ቡድን አስቸጋሪ ጊዜን ከሚሰጡ የሊጉ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ ነው። በተለይ ቡድኑ ከኋላ ረጃጅም እና ተንጠልጣይ እንዲሁም ተከላካካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል እየላከ አደጋን ሲፈጥር ይታያል። ከፊት መስመር አጥቂው ዳዋ በተጨማሪ ደግሞ የመስመር ተጫዋቹ ዱላ ቅልጥፍና ለቡድኑ በጎ ነገሮችን ሲያመጣ ከርሟል። ከዚህ መነሻነት ነገም ቡድኑ በተመሳሳይ አቀራረብ ወደ ሜዳ ሊገባ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም የአማካይ መስመሩን ከአጥቂ መስመሩ ጋር በጥሩ ብቃት የሚያገናኘው አልሀሰን ካሉሻ ቡድኑ መሐል ለመሐልም አደገኛ እንደሆነ የሚያሳይ አቋም ባለፉት ጨዋታዎች ሲያሳይ ተስተውሏል። እርግጥ ተጫዋቹ በዲቻው ጨዋታ ጥሩ ሳይሆን ተቀይሮ ቢወጣም በባለፉት ጨዋታዎች አቋሙ ላይ የሚገኝ ከሆነ ባህር ዳር ከባድ ጊዜን የሚያሳልፍ ይሆናል።

የሊጉ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ባለቤት የሆነው ሀዲያ ሆሳዕና ለወላይታ ዲቻ ሦስት ነጥብ ሲያስረክብ ያሳየው የመከላከል አደረጃጀት ለተጋጣሚ ቡድኖች መልካም ዜናን የሚሰጥ ምሳሌ ነበር። በተለይ ቡድኑ ከማጥቃት ወደ መከላከል ሲያደርግ የነበረው የዘገየ ሽግግር በነገው ጨዋታ ካልታረመ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ስለዚህ ቡድኑ እራሱን ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ አድርጎ መጫወት የለበትም።

በሀዲያ በኩል ለተሻለ ህክምና በመዲናችን አዲስ አበባ ከሚገኘው ቴዎድሮስ በቀለ ውጪ በጨዋታው በጉዳት አልያም በቅጣት የማይኖር ተጫዋች የለም። በተጨማሪም ትላንትና ቡድኑን የተቀላቀለው ዑመድ ኡኩሪ ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን በዛሬው ዕለት ሲሰራ አብሮ ባለመኖሩ በጨዋታው የማይሳተፍ ይሆናል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ዙር ላይ በሊጉን ቀዳሚ ግንኙነታቸውን ሲያደርጉ ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታውን 1-0 ማሸነፍ ችሎ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ሀሪስተን ሄሱ

ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ሳምሶን ጥላሁን

ወሰኑ ዓሊ – ፍፁም ዓለሙ – ግርማ ዲሳሳ

ባዬ ገዛኸኝ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

መሐመድ ሙንታሪ

ሱሌይማን ሀሚድ – ኢሴንዴ አይዛክ – ተስፋዬ በቀለ – ሄኖክ አርፌጮ

ካሉሻ አልሀሰን – ተስፋዬ አለባቸው – አማኑኤል ጎበና

ዱላ ሙላቱ – ዳዋ ሆቴሳ – ቢስማርክ አፒያ


© ሶከር ኢትዮጵያ