ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ15ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ምርጥ አቋማቸውን ያሳዩ ተጫዋቾችን እንዲህ መርጠናል።

አሰላለፍ 3-5-2

ግብ ጠባቂ

ባህሩ ነጋሽ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ለተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታ የመሰለፍ ዕድል ያገኘው ባህሩ በቀጣይ ጨዋታዎችም የጊዮርጊስን ግብ ለመጠበቅ ዕድሉን እንዲያገኝ የሚያስችል ብቃት አስይቷል። ቡድኑ ድሬዳዋን በገጠመበት ጨዋታ ግብ ሳያስተናግድ እንዲወጣ ያደረገ ሲሆን በተለይም የመኸዲን ሙሳ ፣ አስቻለው ግርማ እና ጁኒያስ ናንጄቦን ያለቀላቸው የግብ ሙከራዎች ያዳነበት መንገድ አስደናቂ ነበር።

ተከላካዮች

ከድር ኩሊባሊ – ፋሲል ከነማ

ፈርጣማው የኋላ መስመር ተጫዋች ከድር ቡድኑ ቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪውን ኢትዮጵያ ቡና ገጥሞ ሲያሸንፍ የነበረው ብቃት ልዩ ነበር። በተለይ የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አቡበከር ናስርን እስከ መሀል ሜዳ ድረስ እየመጣ የተቆጣጠረበት መንገድ በጨዋታ ሳምንቱ ከታዩ ምርጥ ተጫዋቾች ውስጥ አንዱ አድርጎታል።

ሰለሞን ወዴሳ – ባህር ዳር ከተማ

በያዝነው የውድድር ዓመት ከመናፍ ዐወል ጋር በፈጠረው ጥምረት በወጥነት ቡድኑን በማገልገል ላይ የሚገኘው ሰለሞን በሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ ንቁ ሆኖ አሳልፏል። ከተጋጣሚው አጥቂዎች ጋር አንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ሲገናኝ የነበረው የበላይነት ባህር ዳርን በተደጋጋሚ ከጥቃት የታደገ ሲሆን የጊዜ አጠባበቁ ጥሩ መሆንም የሀዲያን ቀጥተኛ ጥቃት ዋጋ ያሳጣ ነበር።

ፍሬዘር ካሳ – ድሬዳዋ ከተማ

የድሬዳዋው የተከላካይ መስመር ተጫዋች ፍሬዘር በ14ተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር የነበረበት የብቃት ደረጃ አድናቆት የሚያስቸረው ነበር። ተጫዋቹ የቡድኑን አጠቃላይ የመከላከል መዋቅር ሲመራ እንዲሁም የቀድሜው ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስን የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች በጨዋታው ተፅዕኖ እንዳይፈጥሩ ሲታትርበት የነበረበት መንገድ መልካም ነበር።

አማካዮች

አህመድ ረሺድ – ባህር ዳር ከተማ

በግራ መስመር ተከላካይነት የተሰለፈው አህመድን በሁለቱም መስመሮች የመጫወት አቅሙን ከግምት ውስጥ በማስገባት በቀኝ መስመር ተመላላሽነት ተጠቅመነዋል። ተጫዋቹ ቡድኑ ሀዲያ ሆሳዕናን በረታበት ጨዋታ የተሻለ ጥንካሬ ያለውን የሀዲያን የቀኝ መስመር ጥቃት በማቋረጥ ከፍ ባለ ትኩረት ከመጫወቱ ባለፈ የተሳከት ሸርተቴዎቹ በተለያየ ቅፅበቶች የቡድኑን የኋላ ክፍል እንዳይገለጥ ረድተዋል።

ዳንኤል ደምሴ – ድሬዳዋ ከተማ

ባሳለፍነው ሳምንት ባሳየው ጥሩ አቋም በተጠባባቂነት ይዘነው የነበረው ዳንኤል በዚህ ሳምንት ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ መጥቷል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ እጅግ መልካም ጊዜን ያሳለፈው ተጫዋቹ በተለይ ኳስ በማስጣል እና የተከላካይ መስመሩ ተጋላጭ እንዳይሆን የሰራው ስራ ድንቅ ነበር። አልፎም ተጫዋቹ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በተንጠልጣይ ኳሶች ለአጥቂ መስመር ተጫዋቾቹ ለማድረስ ሲሞክር ተስተውሏል።

ሀብታሙ ተከስተ – ፋሲል ከነማ

ከኳስ ጋር ምቾት ተሰምቶት የሚጫወተው ሀብታሙ ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ጣፋጭ ድል ሲቀዳጅ ያሳየው ብቃት የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ አስገብቶታል። ከምንም በላይ ተጫዋቹ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ኢትዮጵያ ቡናዎች መሐል ለመሐል ጥቃት እንዳይሰነዝሩ ሲጥር ታይቷል። በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ለወትሮው በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የማይቸገረው የተጋጣሚው አጨዋወት አቅም እንዲያጣ የሀብታሙ ሚና የጎላ ነበር።

ኃይለሚካኤል አደፍርስ – ሰበታ ከተማ

የቀኝ መስመር ተከላካዩ ኃይለሚካኤልን በመረጥነው አደራደር ውስጥ የተመላላሽነት ሚና ሰጥተነዋል። ቡድኑ ሀዋሳ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ የተጋጣሚው ጠንካራ ጎን የሆነውን የመስመር ጥቃት ከመከላከል ባለፈ ወደ ፊት በመሄድ በማጥቃቱ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ድፍረቱ የነበረው ተጫዋቹ የቴክኒክ ብቃቱን በሚያሳይ መልኩ ለፍፁም ገብረማርያም ጎል መገኘት ምክንያት የሆነችን ኳስ አመቻችቷል።

መስዑድ መሐመድ – ሰበታ ከተማ

ከተከላካዮች ፊት ባለው ቦታ ላይ በብቸኝነት ወይም ከሌላ አጣማሪ ጋር ሲሰለፍ የቆየው መስዑድ በቅርብ ጨዋታዎች ለተጋጣሚ የግብ ክልል ቀርቦ እየተጫወተ ይገኛል። በሚና ለውጡ በተሰጠው ጨዋታ በማቀጣጠል ኃላፊነቱ የሰበታን እንቅስቃሴ በጥሩ ሁኔታ በመራበት በዚህ ሳምንት በሀዋሳ ተከላካዮች መሀል በመግባት በሳጥን ውስጥ በተገኘበት አጋጣሚ በድንቅ አጨራረስ ለቡድኑ ድል ልዩነት የፈጠረችዋን ጎል ማስቆጠርም ችሏል።

አጥቂዎች

ሙጂብ ቃሲም – ፋሲል ከነማ

የፊት አጥቂዎች ጎልተው ባልወጡበት በዚህ ሳምንት ከግብ አግቢነቱ ርቆ የሰነበተው ሙጂብ ዳግም ተመልሷል። ለአራት ጨዋታዎች ኳስ እና መረብን ማገናኘት ተስኖት ከመቆየቱ ባለፈ ፋሲል ኢትዮጵያ ቡናን የገጠመበት ጨዋታ ከነበረ ተጠባቂነት አንፃር ሙጂብ ከፍ ባለ ጫና ውስጥ ጨዋታውን ቢያደርግም ኃላፊነቱን ተአጥቶ ፋሲልን ባለድል ያደረገችውን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል።

ፍፁም ገብረማርያም – ሰበታ ከተማ

በቅርብ ጨዋታዎች ግቦችን በማስቆጠር እያንሰራራ የሚገኘው ፍፁም በዚህ ሳምንትም ሰበታ በወሳኝ ሰዓት አጋማሹን በመሪነት እንዲዘጋ ያስቻለች ጎል አስቆጥሯል። የመጨረሻ የዘጠኝ ቁጥር ባህሪ የተላበሰ አጥቂ መሆኑን በተደጋጋሚ እያሳየን የሚገኘው ፍፁም ሀዋሳ ላይም በተመሳሳይ ሳጥን ውስጥ በትክክለኛው ቦታ ላይ በመገኘት ተከላካዮችን በጫና ውስጥ እንዲቆዩ አድርጓል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ

በዚህ ሳምንት ከተመዘገቡ ድሎች ሁሉ ፋሲል ከነማ በኢትዮጵያ ቡና ላይ እንዳገኘው ድል ወሳኝ አልነበረም። አሰልጣኝ ሥዩም የተጋጣሚያቸውን ጥንካሬ ከቡድናቸው አቅም ጋር ባገናዘበ መልኩ በሁለቱ አጋማሾች የተለያዩ አቀራረቦችን በመከተል እጅግ ወሳኝ የሆነውን ድል በማሳካት ሊጉን በስምንት ነጥቦች ልዩነት መምራት ጀምረዋል።

ተጠባባቂዎች

አቡበከር ኑሪ – ጅማ አባ ጅፋር
አስቻለው ታመነ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ያሬድ ዘውድነህ – ድሬዳዋ ከተማ
ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ
ጋቶች ፓኖም – ወላይታ ድቻ
በኃይሉ ተሻገር – ወልቂጤ ከተማ
አስቻለው ግርማ – ድሬዳዋ ከተማ


© ሶከር ኢትዮጵያ