” አሁን ካለንበት ደረጃ በላይ መቀመጥ ይገባን ነበር ” – ሰለሞን ወዴሳ

ዛሬ ከሰዓት ባህር ዳር ከተማ አዳማ ከተማን አንድ ለምንም በረታበት ጨዋታ ላይ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ሰለሞን ወዴሳ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታን አድርጓል።

በመቀመጫ ከተማቸው ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች አስሩን ያሳኩት ባህር ዳር ከተማዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተከታታይ ያሸነፏቸውን ጨዋታዎች ቁጥር ሦስት አድርሰዋል። ቡድኑ ድል ባገኘባቸው ያለፉት ሦስት ጨዋታዎች ድንቅ ብቃታቸውን ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል የመሐል ተከላካዩ ሰለሞን ወዴሳ ተጠቃሽ ነው። በሀዋሳ ከተማ አድጎ ወደ ኢትዮጵያ መድን በማቅናት ራሱን ካጎለበተ በኋላ ወደ ባህር ዳር የመጣው ይህ ወጣት እና ቀልጣፋ ተከላካይ ስለ ዛሬው ጨዋታ፣ ስለቡድኑ የአሸናፊነት ጉዞ እና ወቅታዊ ብቃቱ ተከታዩን ብሎናል።

“የዛሬው ጨዋታ በጣም አሪፍ ነበር። ተከታታይ ሦስተኛ ድላችንንም ነው ዛሬ ያስመዘገብነው። በእንቅስቃሴ ደረጃም የነበረን ነገር እጅግ ጥሩ ነበር። ተጋጣሚያችን አዳማም ምንም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርግ ነው የወጣው።

“እንደሚታወቀው ባህር ዳር ከመጣን በኋላ ከውጤት መጥፋት ጋር ተያይዞ ብዙ ጫናዎች ነበሩብን። እኛም ውጥረት ውስጥ ገብተን ነበር። ግን ተነጋግረን ያለውን ነገር ለማስተካከል ሞከርን። በተለይም ቡድኑ ግብ እንዳያስተናግድ ስንሰራ ነበር። ይህም ተሳክቶልን ባህር ዳር ላይ ካደረግናቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ አስተናግደን (እርሱንም በፍፁም ቅጣት ምት) ወጥተናል። በአጠቃላይ የቡድኑ የኋላ መስመር ከባለፈው ዓመት በተሻለ ጥንካሬ ላይ ይገኛል። አሁን መስራት ያለብን ግብ ማስቆጠሩ ላይ ነው።

“ከመናፍ ጋር ያለን ጥምረት እጅግ አሪፍ ነው። እንደምታቁት የሊጉ ሦስተኛው ትንሽ ጎል የተቆጠረበት ቡድን ባለቤት ነን። ከተቆጠሩብን ጎሎች ውስጥም የፍፁም ቅጣት ምቶች አሉ። በአጠቃላይ ግን መናፍም ሆነ እኔ እየተግባባን ነው የምንጫወተው። ገና ባህር ዳር መናፍ መጣ ሲባልም በጣም ነበር ደስ ያለኝ። ሁለታችንም ወጣት መሆናችን ደግሞ ጠቅሞናል።

“ያለን የተጫዋቾች ስብስብ በጣም አሪፍ ነው። የውጤት ነገር ሆነ እንጂ አሁን ካለንበት ደረጃ በላይ መቀመጥ ይገባን ነበር። ከዚህ በኋላም ከበላያችን ያሉትን ክለቦች ማየት ሳይሆን ፊት ለፊታችን ያሉትን ጨዋታዎች ማሸነፍ የሚኖርብን ይመስለኛል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ