​የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-1 ባህር ዳር ከተማ

ከከሰዓቱ ጨዋታ በኋላ የተጋጣሚ አሰልጣኞች እና የሱፐር ስፖርት ቆይታ ይህንን መሳይ ነበር።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – አዳማ ከተማ

ስለጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ያልነበርንበት ነው። በተለይ ከዕረፍት በኋላ ብዙ ኳሶችን መጠቀም ይችሉ ነበር ፤ አልተጠቀሙም። ቡድኑ ላይ በተለይ በሥነ-ልቦናው በኩል በጣም ቶሎ ነው የሚወርዱት ልጆቹ። በዛ ላይ የአካል ብቃት ችግርም ይታያል። ብዙ ክፍተቶችን ነው እንዲያውም ዛሬ ለማየት የሞከርኩት። ቡድኑ ብዙ ነገር እንደሚቀረው ነው የተረዳሁት። እንደቡድን ባህር ዳር ወደ ፊት ሲሄዱ ጥሩ ነበሩ። የእኛ ደግሞ በተቃራኒው ከኋላ የነበሩ ልጆች ተከላካይ አማካይ ሆነው የሚጫወቱ ናቸው እና ቦታው ላይ ሰው ስለሌለ የግዴታ የተጠቀምናቸው ለዛ ነው። በተደጋጋሚ ያው ያንን ስህተት ነው ሲሰሩ የነበሩት። ዞሮ ዞሮ ቡድኑ ብዙ መስተካከል እንዳለበት ነው የሚሰማኝ። 

ተከታታይ ሽንፈት በአሰልጣኝ ላይ ስለሚፈጥረው ስሜት

አዎ በጣም ፤ ምክንያቱም ለማስተካከል ትቸገራለህ። አዳማ ከጅምሩ እስካሁን የመጣበት መንገድ ያ ቢሆንም እኔ በግሌ ይሄ ነገር በተደጋጋሚ ባያጋጥመኝም መስራት እንዳለብን ነው የሚሰማኝ። መጀመሪያም አምኜበት ስለሆነ ቡድኑ ያለበት ቦታ ከባድ ስለሆነ ያንን ለመቅረፍ ነበር ሀሳቤ። ግን ያው ተጫዋቾቹ ጋር ያገኘሁት ነገር በተቃራኒው ነው። ስለዚህ ዞሮ ዞሮ ወደ ፉክክሩ ለመምጣት ወይም ወደ ላለመውረድ ለመምጣት ቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች እንያንዳንዱ ጨዋታ እንደ ፍፃሜ የሚቆጠር ጨዋታ ነው። ስለዚህ እዛ ላይ ነው ጠንክረን የምንሰራው። መጀመሪያም ያው ሦስቱ ጨዋታ ላይ እንደምቸገር ግልፅ ነው። በተደጋጋሚ ለሚዲያም ገልጫለሁ። አስቸጋሪ እንደሚሆንብኝ አውቃለሁ ግን ቢያንስ ነጥብ ተጋርተን ለመውጣት ነው ሦስቱንም ጨዋታዎች ጥረት ያደረግነው። ግን ዞሮ ዞሮ አልተሳካም በጥቃቅን ስህተቶች ጎሎች ይገቡና ተሸንፈን እየወጣን ነው። 

የብሔራዊ ቡድን ዕረፍት 

ይሄ አንደኛ ዙር እንዳለቀ ውድድሩ ቆሞ ቢሆን ኖሮ ብዙ መስተካከል የሚችሉ ነገሮች ነበሩ። ዕረፍቱ አዳማን ጠንክሮ እንዲመጣ ይረዳዋል ብዬ ነው የማስበው። ከምንም በላይ ለአዳማ በጣም ወሳኝ ነው ብዬ ነው የማስበው ፤ ይጠቅመናል ብዬ ነው የማስበው። 

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ባህር ዳር ከተማ ቆይታቸው 

ከሞላ ጎደል የተሻለ ነበር ፤ ጥሩ ነው እላለሁ። በዛሬውም ጨዋታ የምንፈልገውን ሦስት ነጥብ አግኝተናል። በተለይ በሁለተኛው 45 ብዙ የግብ ዕድሎች ፈጥረናል። አሁንም ያገኘናቸውን ዕድሎች ያለመጠቀም ስህተታችን እንዳለ ነው። በሚቀጥለው በድሬዳዋ በሚኖረን ውድድር ላይ በተቻለን መጠን ለማሻሻል እንሞክራለን። ዋናው ነገር ግን ጨዋታውን ተቆጣጥረን ተጫዋቾቼ ዘና ብለው ሲጫወቱ ማየቴ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ።

በቀጣዮቹ ጨዋታዎች የቡድኑ ህልም

እንግዲህ ደረጃችንን ከፍ ማድረግ ነው። ምንም እንኳን ፋሲል በነጥብ ራቅ ያለንም ቢሆን በእግር ኳስ ምን እንደሚፈጠር ስለማይታወቅ እኛ በየቀኑ የየቀኑ ጨዋታዎቻችንን ማሸነፍ እንሞክራለን። መጨረሻ ላይ የሚመጣውን ውጤት እንቀበላለን።

ስለአጥቂዎች አጨራረስ

ዋናው መጀመሪያ የግብ ዕድሎችን መፍጠራችን እንደቡድን ትልቅ ነገር ነው ብዬ አስባለሁ። አንዳንድ ጨዋታዎች ላይ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ተቸግረን ነበር። ግን እያሸነፍን ስንመጣ የተጫዋቾቻችን ሥነ-ልቦና ከፍ ሲል የሚፈልጉትን እያደረጉ ነው። ስለዚህ የጎል ዕድሎችን አግኝተናል። ግን ብዙ መስራት ይጠበቅብናል። ከፊት ያሉን አጥቂዎች ምንይሉም ሆነ ባዬ ልምድ ያላቸው ጥሩ ጎል አግቢዎች ናቸው። ያንን ሥነ- ልቦናቸውን መመለስ ላይ ጠንክረን እንሰራለን ብዬ አስባለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ