ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ በከተማቸው የነበራቸውን ቆይታ በድል ዘግተዋል

በአዳማ እና ባህር ዳር ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ በባህር ዳር አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

አዳማ ከተማዎች በወላይታ ድቻ አንድ ለምንም ከተረቱበት ጨዋታ ሁለት ተጫዋቾችን ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም በጨዋታው አስደንጋጭ አደጋ አጋጥሞት የነበረውን ታሪክ ጌትነትን እና በቃሉ ገነነን በዳንኤል ተሾመ እና እዮብ ማቲዮስ ተክተዋል። አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው የውድድር ዓመቱን ተከታታይ ድል ካገኙበት የሀዲያው ጨዋታ ግርማ ዲሳሳን በሣለአምላክ ተገኘ ብቻ ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።

ጨዋታውን በተሻለ ተነሳሽነት የጀመሩት ባህር ዳር ከተማዎች የሚያገኟቸውን ኳሶች በትዕግስት በመቀባበል ወደ ግብነት ለመቀየር ሲጥሩ ተስተውሏል። በተቃራኒው ከኳስ ጀርባ በመሆን የጨዋታውን የመጀመሪያ ደቂቃ የተጫወቱት አዳማዎች በ5ኛው ደቂቃ የባህር ዳር ተከላካዮች የሰሩትን የኳስ ቅብብል ስህተት ተጠቅመው በአምበላቸው ኤልያስ ማሞ አማካኝነት የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ (ዒላማውን ያልጠበቀ) ሰንዝረዋል። ይህንን ሙከራ ካደረጉ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም አብዲሳ ጀማል ከመዕዘን የተሻማውን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየት ሲሞክር የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል በድጋሚ ፈትሸዋል።

የኳስ ቁጥጥር የበላይነታቸውን በጎል ለማጀብ የፈለጉት ባህር ዳር ከተማዎች በ13ኛው ደቂቃ አህመድ ረሺድ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት በሳምሶን ጥላሁን አማካኝነት አሻምተውት የቡድኑ አምበል ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ጥሮ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ከደቂቃ በኋላም ወሰኑ ዓሊ በግራ መስመር ከሳምሶን የተቀበለውን ኳስ መረብ ላይ ለማሳረፍ ጥሮ መክኖበታል።

አሁንም ጥቃት መሰንዘራቸውን ያላቆሙት የጣና ሞገዶቹ የጥረታቸውን ፍሬ በ22ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። በዚህም ፍፁም ዓለሙ ከባዬ ገዛኸኝ የተቀበለውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ዳንኤል መረብ ላይ አሳርፎት መምራት ጀምረዋል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ዘጠኝ ደቂቃዎች ሲቀሩትም በድጋሚ በፈጣን ሽግግር አዳማ የግብ ክልል ደርሰው ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። አዳማዎችም በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ያገኙትን የግብ ማግባት አጋጣሚ መድገም ሳይችሉ አጋማሹ በባህር ዳር ከተማ አንድ ለምንም መሪነት ተገባዷል።

ሁለት ተጫዋቾችን በመለወጥ አጋማሹን የጀመሩት አዳማ ከተማዎች በቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያስችላቸውን ግብ ፍለጋ ረጃጅም ኳሶችን መጠቀም ምርጫቸው በማድረግ ሲጫወቱ ተስተውሏል። በአንፃሩ ተጋጣሚያቸው ግብ ፍለጋ የገባበት ውጥረት የጠቀማቸው ባህር ዳሮች ከተከላካይ ጀርባ የሚያገኙትን ሜዳ በፈጣኖቹ ተጫዋቾች በመጠቀም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። በ49ኛው ደቂቃም የግብ ዘቡ ዳንኤል የተሳሳተውን ኳስ ሣለአምላክ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ በማግኘት ጥሩ ሙከራ ሰንዝሯል። ነገር ግን ስህተቱን ለማረም ጊዜ ያገኘው ዳንኤል አጋጣሚውን በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖታል።

ጨዋታው ቀጥሎም በ64ኛው ደቂቃ ባህር ዳሮች እጅግ ለግብነት የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። በዚህም በፈጣን ሩጫ በቀኝ መስመር የገባው የግቡ ባለቤት ፍፁም ተቀይሮ ለገባው ምንይሉ ወንድሙ ጥሩ ኳስ አመቻችቶ ምንይሉ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። እንዳሰቡት የባህርዳርን የግብ ክልል ማስከፈት ያልቻሉት አዳማዎች በ70ኛው ደቂቃ አቻ የሚሆኑበትን ጥሩ ኳስ ወደ ግብ ልከው ነበር። በዚህ ደቂቃም ተከላካዮች በግንባራቸው ገጭተው ያወጡትን ኳስ ኤልያስ ማሞ ከሳጥን ውጪ ወደ ጎል መትቶት ለጥቂት ወጥቶበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ገብቶ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ሲያገኝ የነበረው ነገር ግን አጋጣሚዎቹን ወደ ግብነት መቀየር የተሳነው ምንይሉ በ73ኛው ደቂቃ እጅግ አስቆጪ ኳስ ብቻውን አግኝቶ አምክኗል። በጨዋታው ከፍተኛ ብልጫ የነበራቸው ባህርዳሮች ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ በቀሩት ጥቂት ደቂቃዎች አራት ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን በዜናው፣ ምንይሉ እና ሣለአምላክ አማካኝነት አግኝተው ነበር። ጨዋታው የከበዳቸው የሚመስለው አዳማዎች በጨዋታው ምንም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ከሜዳ ወጥተዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በባህር ዳር ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ በጨዋታው ሦስት ነጥብ ያገኙት ባህር ዳር ከተማዎች ነጥባቸውን 26 በማድረስ ሦስተኛ ደረጃን አንድ ጨዋታ ከሚቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተረክበዋል። በተቃራኒው የውድድር ዓመቱን 12ኛ ሸንፈታቸውን ያስመዘገቡት አዳማ ከተማዎች በ7 ነጥብ የደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ (13) ላይ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ