ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የሴናፍ ዋቁማ የቅጣት ምት ጎል መከላከያን ሦስት ነጥብ አስጨብጣለች

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የአስራ ስድስተኛ ሳምንት ሦስተኛ ጨዋታ ረፋድ ላይ ተደርጎ የሴናፍ ዋቁማ የቅጣት ምት ጎል መከላከያ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1ለ 0 እንዲያሸንፍ አስችሏል፡፡

መከላከያ በቻምፒዮንነት ፉክክር ውስጥ የሚገኝ ከመሆኑ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካለው ሰሞነኛ ውጤታማነቱ መነሻነት ጨዋታው አስቀድሞ ተጠባቂ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ተመጣጣኝ የሆነ ፉክክርን ባስተዋልንበት ቀዳሚው የጨዋታው አርባ አምስት መከላከያዎች አብዛኛዎቹን እንቅስቃሴያቸውን መሀል ሜዳ ላይ በማድረግ ወደ አጥቂ ክፍሉ በሚገኙ ክፍተቶች ኳስን በማሳለፍ ለማጥቃት ይዘው የገቡት የጨዋታ መንገድ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው ወደ የኮሪደር አጠቃቀማቸውን በይበልጥ በመጠቀም ከእፀገነት ብዙነህ እግር ስር ከሚነሱ ኳሶች ወደ ታታሪዋ አጥቂ ዮርዳኖስ ምዑዝ ቶሎ ቶሎ በመጣል ግብ ለማግኘት ጥረዋል፡፡

በሲሳይ ገብረዋህድ ወደ ጎል በመጠጋት ቀዳሚ መሆን የቻሉት ኤሌክትሪኮች ጠንካራ ሙከራን ዳግም 12ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። እፀገነት ብዙነህ በቀኝ የመከላከያ የግብ ክልል የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ጎል ስታሻማ ግዙፏ ተከላካይ መሰሉ አበራ በግንባር ገጭታ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣባት አጋጣሚ ሌላኛው የቡድኑ ሙከራ ነበር፡፡

በሒደት ጥቃት ወደ መሰንዘሩ የገቡት መከላከያዎች 21ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ሙከራቸውን አድርገዋል፡፡ በመልሶ ማጥቃት ከግራ የኤሌክትሪክ ግብ ክልል ሴናፍ ዋቁማ የሰጠቻትን ኳስ መዲና ዐወል በቀጥታ ስትመታው የግቡን ቋሚ ታካ ኳሷ ወጥታባታለች፡፡ ከዚህች አጋጣሚ በኃላ 32ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ሴናፍ ዋቁማ በቀጥታ ወደ ግብ አክርራ መታ የግቡ ቋሚ ብረት መልሶባታል፡፡

ከ35ኛው ደቂቃ በኃላ ከቆመ ኳስ ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉበትን የጨዋታ መንገድ በሚገባ ተመልክተናል፡፡ 36ኛው ደቂቃ የኢትዮ ኤሌክትሪኳ አምበል እታፈራሁ አድርሴ በራሷ የግብ ክልል አካባቢ ከመከላከያዋ የመስመር ተጫዋች መሳይ ተመስገን ጋር ተጋጭታ በመውደቋ ያስተናገደችሁም ጉዳት ጠንከር ያለ በመሆኑ በአምቡላንስ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሆስፒታል አምርታለች፡፡

ጨዋታው ቀጥሎ 39ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግዷል፡፡ ከሳጥን ውጪ በኤሌክትሪክ ግብ ትይዩ መዲና ዐወል ላይ ተከላካዮች የሰሩት ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት በግምት ከሀያ አምስት ሜትር ርቀት ሴናፍ ዋቁማ በትዕግስት አበራ መረብ ላይ በማሳረፍ መከላከያን መሪ አድርጋለች፡፡

ቡድኖቹ ከእረፍት ሲመለሱ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፍፁም የጨዋታ እና የሙከራ ብልጫን ይዘው የተመለሱበት ነበር፡፡ በአንድ ሁለት ቅብብል በይበልጥ የመስመር ተጫዋቾቻቸውን ሲጠቀሙ የታየው ቡድኑ በተደጋጋሚ አቻ ለመሆን የመከላከያን ተከላካዮች ሲፈትኑ ተስተውሏል፡፡በተለይ ከሁለቱም የመስመር ቦታዎቻቸው ወደ ሳጥን ተጫዋቾቻቸውን በማስጠጋት በሣራ ነብሶ እና ዮርዳኖስ ምዑዝ አማካኝነት ግብ ለማግኘት ጥረት የጀመሩት ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ነበር፡፡

ዮርዳኖስ ምዑዝ በረጅሙ ያገኘችውን ኳስ ከግብ ጠባቂዋ ታሪኳ በርገና ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ ኳሷን ብትመታውም ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውባታል፡፡ መከላካያዎች ለማጥቃት የነበራቸው ጥንካሬ ወጥነት ይጎለው ስለነበር ኳሳቸው የኤሌክትሪክ የግብ ክልል ከደረሰ በኃላ በቶሎ ይነጠቁ ስለነበር ተጨማሪ ግብ ለማከል አላደላቸውም፡፡

በመሰሉ አበራ ሶስት የቅጣት ምት ኳሶች በተደጋጋሚ ወደ ጎል መቅረብ የቻሉት ኤሌክትሪኮች የአጨራረስ ችግር ካልሆነ በቀር ያለቀላቸውን ዕድል በማግኘት የሚስተካከላቸው አልነበረም፡፡ 60ኛው ደቂቃ ዮርዳኖስ ምዑዝ የግል ጥረቷን ተጠቅማ የሰጠቻትን ኳስ ሳራ ነብሶ በቀላሉ አስቆጠረችሁ ሲባል አምክናዋለች፡፡

የመጨረሻዎቹን አስራ አምስት ደቂቃ መከላከል ላይ አመዝነው የታዩት መከላከያዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ያስቆጠሩትን አንድ ግብ ለማስጠበቅ ጥረት አድርገዋል፡፡ መደበኛው ዘጠና ደቂቃ ተጠናቆ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በሰጠችው የጭማሪ ደቂቃ ላይ መሰሉ አበራ አክርራ ወደ ጎል ከቅጣት ምት መታ ታሩኳ በርገና የያዘችባት ኳስ መስመር አልፏል በሚል የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች ቅሬታ ሲያሰሙ የታየ ቢሆንም የዕለቱ ዋና ዳኛ ጨዋታውን በሁለተኛ ቅጣት ምት እንዲጀምር በማድረግ ጨዋታው 1ለ0 ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ መከላከያም ሀዋሳ ከደቂቃዎች በኃላ ከንግድ ባንክ ጋር እስኪጫወት ድረስ ደረጃውን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ