ዋልያዎቹ የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅታቸውን ጀመሩ

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅቱን በባህር ዳር ጀምሯል።

የመጀመርያው እና ሁለተኛ ምዕራፍ ዝግጅታቸውን በጅማ እና በአዲስ አበባ ያደረጉት ዋልያዎቹ በቀጣይ ለሚጠብቃቸው ወሳኝ አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅታቸውን በዛሬው ዕለት አስር ሰዓት ላይ በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ሜዳ ጀምረዋል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በአዲስ መልክ ጥሪ ከቀረበላቸው 25 ተጫዋቾች ውስጥ ለግብፁ ምስር አልመቃሳ ከሚጫወተው ሽመልስ በቀለ በቀር ሁሉም የቡድኑ አባላት በመጀመርያ ቀን ልምምድ ተሳትፈዋል። በክለባቸው አገልግሎት እየሰጡ ባለበት ወቅት በጉዳት ተቀይረው የወጡት የወልቂጤዎቹ ረመዳን ናስርና አብዱልከሪም ወርቁም በዛሬው ልምምድ ተካተው ሠርተዋል።

በብሉ ናይል(አቫንቲ) ሆቴል ማረፍያውን ያደረገው ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣይ ረቡብ ከማላዊ ጋር ለሚያደርገው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በማሰብ እና ተጫዋቾቹ ከነበረባቸው ድካም አንፃር በዛሬው በዛሬው ዝግጅታቸው ከኳስ ጋር ቀለል ያለ ልምምድ ሲሰሩ ተስተውሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ ጨዋታውን በመጋቢት 15 ቀን በባህር ዳር ከማዳጋስካር ጋር ያደርግና ከስድስት ቀን በኃላ መጋቢት 21 ኮትዲቯር ጋር በአቢጃን እንደሚጫወቱ ይታወቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ