ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያዎች በዋንጫው ፉክክር የሚያቆያቸውን ድል አስመዘገቡ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአስራ ሰባተኛ ሳምንት ሁለተኛ መርሀግብር ድሬዳዋ ከተማን ከ መከላከያ አገናኝቶ የሥራ ይርዳው ጎል መከላከያን 1ለ0 አሸናፊ አድርጓል።

የመጀመሪያዎቹን ሀያ ደቂቃዎች መከላከያዎች ኤደን ሺፈራው እና ህይወት ረጉን ማዕከል ባደረገ የመሐል ሜዳ እንቅስቃሴ አመዝኘው የታዩ ሲሆን ረጃጅም ኳሶችን ወደ ግራ መስመር ተሰላፊዋ መሳይ ተመስገን በመጣል ተጫዋቿም ወደ ሥራ እና ሴናፍ በማሻማት ዕድሎችን ለመፍጠረት ጥረት አድርገዋል። በዚህ ሒደት ሥራ ይርዳው ከተጫዋቿ ባገኘችው ኳስ 24ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግብ ክልል መጠጋት የቻለው ክለቡ 30ኛው ደቂቃ ላይም ሌላ ሙከራን ፈጥሯል፡፡ መሳይ ተመስገን ከማዕዘን ስታሻማ ሴናፍ በግንባር ገጭታ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታኮ የወጣበት አጋጣሚም የተሻለው የክለቡ ሙከራ ነበረች፡፡ ማዕድን ሳህሉ 40ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አክርራ መታ ታሪኳ በርገና ከመለሰችባት ኳስ ውጪ የጠራ ሙከራን ድሬዳዋዎች መፍጠር ተስኗቸዋል፡፡

ክለቦቹ ከእረፍት ሲመለሱ መከላከያዎች በተሻለ የሜዳ ላይ ቆይታን ሲያደርጉ የተስተዋለበት ድሬዳዋዎች በበኩላቸው ቁምነገር ካሳን ብቻ ዋነኛ ትኩረታቸው አድርገው የተንቀሳቀሱበት ነበር፡፡ ቶሎ ቶሎ ፈጣን እንቅስቃሴን ተግባራዊ ያደረጉት መከላከያዎች 60ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል፡፡ በግራ የድሬዳዋ የግብ ክልል አካባቢ የተገኘውን የቅጣት ምት መሳይ ተመስገን ወደ ጎል በረጅሙ ስታሻማ ሴናፍ በግንባር ወደ ጎሉ ልትወጣ ያለችውን ኳስ ስትመልስ ሥራ ይርዳው አግኝታው በግንባር ገጭታ በቀድሞው ክለቧ መረብ ላይ አሳርፋ ክለቧን መሪ አድርጋለች።

ከግቧ መቆጠር በኃላ በአንድ ሁለት ቅብብል ህይወት ረጉ እና ሥራ ይርዳው በፈጠሩት ቅንጅት በመጨረሻም ስራ ለሴናፍ ሰጥታት ስትመታው ለጥቂት ከግቡ ቋሚ ብረት ስር ወጥቶባታል፡፡

ከአጥቂዋ ቁምነገር ካሳ ጎል ለማግኘት ብቻ በሚመስል መልኩ የተንቀሳቀሱት ድሬዳዋዎች ተጫዋቾችንም ለውጠው ቢያስገቡ ከቁምነገር ጥገኝነት ሊወጡ አልቻሉም፡፡ 72ኛው ደቂቃ ላይ ቁምነገር ከማዕድን በመከላከያ ተከላካዮች መሀል ለመሀል የተሰጣትን ኳስ ወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ ወደ ጎል መታው ግብ ጠባቂዋ ታሪኳ በርገና የያዘችባት ድሬዎች ያደረጓት ብቸኛ ሙከራ ነች፡፡

መደበኛው የጨዋታው ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠ ጭማሪ ሰአት ህይወት መሀል ለመሀል አሾልካ ሰጥታ ሴናፍ ወደ ጎል ስትመታው ሂሩት ያወጣችባት መከላከያ ሁለተኛ ግብ የሚያገኙበት አጋጣሚ ቢሆንም ወደ ጎልነት ሳይለወጥ ጨዋታው 1ለ0 በሆነ ውጤት መከላከያ አሸንፎ ወጥቷል፡፡ መከላከያም ነገ ባንክ ጨዋታ እስኪያደርግ ድረስ በዋንጫ ፉክክሩ የቆየበትን ድል ማግኘት ችሏል።

10፡00 ሲል ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሳምንቱ ሌላ ጨዋታ የሚቀጥል ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ