ፈረሰኞቹ የቀድሞ ምክትል አሠልጣኛቸውን ወደ ዋናው ቡድን መልሰዋል

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የምክትል አሠልጣኝ ሹመት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ለበርካታ ዓመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ውስጥ በተጫዋችነት እና በምክትል አሠልጣኝነት ያገለገለው ዘሪሁን ሸንገታ ከዋና ቡድኑ ገለል ብሎ በተስፋ ቡድን ውስጥ ብቻ እንዲያገለግል ክለቡ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። ወሳኔውን ተከትሎም በቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን ግልጋሎት እየሰጠ የነበረው አሠልጣኙ በዛሬው ዕለት ዳግም ወደ ዋናው ቡድን ተመልሶ በምክትል አሠልጣኝነት እንዲያሰለጥን ተወስኗል። የማሒር ዴቪድስ ምክትል ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አሠልጣኝ ደረጄ ደግሞ ወደ ተስፋ ቡድኑ ወርደው እንዲሰሩ ተወስኗል።

በተያያዘ ዜና ዋና አሠልጣኛቸው ማሒር ዴቪድስን ለእረፍት የሸኙት ፈረሰኞቹ ሰኞ ወደ መደበኛ ልምምዳቸው እንደሚመለሱ ለማወቅ ተችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ