አዳማ ከተማ የግብ ዘብ አስፈርሟል

በዝውውር ገበያው በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች በዛሬው ዕለትም የውጪ ዜጋ ግብ ጠባቂ ማስፈረማቸው ታውቋል።

በዘንድሮው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ደካማ እንቅስቃሴን በማሳየት የወራጅ ቀጠናው ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች በቀሪ የሊጉ ጨዋታዎች ተጠናክረው በመቅረብ ካሉበት ደረጃ ለመሻሻል አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው እየቀላቀሉ ይገኛሉ። ከትላንት በስትያ አራት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን የግሉ ያደረገው ቡድኑ ዛሬም ተጨማሪ ተጫዋች ማስፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋች ጊኒያዊው ሴኩምባ ካማራ ነው። 1.93 ሜትር የሚረዝመው የግብ ዘቡ ከዚህ ቀደም ለጊኒው አትሌቲኮ ዴ ኮናክሪ፣ ለእስራኤሉ ሃፖኤል ራናና ለጊኒው ኤ ኤስ ካሉም ተጫውቶ አሳልፏል። ቁመታሙ ሴኩምባ ጊኒ ወደ ቻን ስታልፍም ሦስት ፍፁም ቅጣት ምቶችን በማዳን ትልቁን ድርሻ ተወጥቶ ነበር፡፡ በዛሬው ዕለትም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የአሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን ስብስብ በይፋ ተቀላቅሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ