ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን የሚያድገው ሁለተኛ ቡድን ታውቋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ባህር ዳር ከተማን ተከትሎ ወደ አንደኛው ዲቪዝዮን ያደገው ቡድን ተለይቷል።

ዛሬ ጠዋት 2፡00 ላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ እና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ተገናኝተው 1ለ1 በሆነ ውጤት የዓመቱ ጨዋታቸውን ፈፅመዋል፡፡ ጥሩነሽ ዲባባዎች ገና ጨዋታው እንደ ተጀመረ በዕድላዊት ቢኒያም ጎል መሪ መሆን ቢችሉም ከእረፍት መልስ ንግስት በቀለ ለወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው 1ለ1 ፍፃሜን አግኝቷል፡፡

ከሰዓት 10፡00 ሲል በተለያዩ ሜዳዎች ባህር ዳር ከተማን ተከትለው ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን የማደግ ዕድል የነበራቸው ቦሌ ክፍለ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታዎቻቸውን አከናውነዋል፡፡ በሀዋሳ ደቡብ ኮሌጅ ሜዳ ላይ ቦሌ ክፍለ ከተማ ከሻሸመኔ ከተማ ጋር ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ የሻሸመኔ ከተማ ክለብ ተጫዋቾች በስታዲየሙ መገኘት ባለመቻላቸው በህጉ መሠረት የዕለቱ ዳኞች ሰላሳ ደቂቃ ከጠበቁ በኃላ በሜዳ ላይ ለተገኘው ቦሌ ክፍለ ከተማ የፎርፌ ውጤት ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ የፎርፌ ተሸናፊሆነው የሻሸመኔ ቡድንም ጨዋታውን ባለማድረጉና በሌሎች ቡድኖች ውጤት ላይ ተፅእኖ በማሳረፉ የስልሳ ሺህ ብር ቅጣትን ጨምሮ የቡድን መሪ እገዳ እና ሌሎች በውድድር ደንቡ መሰረት ከፍ ያለ ቅጣት እንደሚጠብቀው ለማወቅ ችለናል።

ይህንን የፎርፌ ውጤት መነሻ በማድረግ 36 ነጥቦች የነበሩት ቦሌ ነጥቡን 39 በማድረስ ባህር ዳር ከተማን ተከትሎ በ2014 በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተወዳዳሪ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

በ35 ነጥቦች ቦሌ ክፍለ ከተማን ይከተል የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ንፋስ ስልክ ጋር በተመሳሳይ ሰዓት በሀዋሳ አርቴፊሻል ሳር ሜዳ ላይ ጨዋታውን አከናውነዋል፡፡ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፍቅርአዲስ ተስፋዬ በመጀመሪያው እና የመጨረሻ የጭማሪ ደቂቃ ሁለት ጎል ስታስቆጥር ለንፋስ ስልክ ቻይና ግዛቸው ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በፈረሰኞቹ እንስቶች 2-1 አሸናፊነት ተገባዷል፡፡ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን 38 ያደረሱት ጊዮርጊሶች ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን የማደግ ተስፋቸው በቦሌ በአንድ ነጥብ ተቀድመው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

የሊጉ የመዝጊያ ጨዋታዎች ነገ ሲደረጉ ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ልደታ 2:00፣ ቻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው ባህር ዳር ከተማ ደግሞ 04:00 ላይ ቂርቆስን የሚገጥም ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ