የአዲስ አበባ ከ17 ዓመት በታች ውድድር የሁለተኛ ሳምንት ውሎ

ሁለተኛ ሳምንቱን ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች ውድድር በዛሬው ዕለት በስድስት ጨዋታዎች ቀጥሏል።

አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ በሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው የጠዋት ሦስት ሰዓት ጨዋታ እጅግ አዝናኝ በሆነ ሁኔታ አፍሮ ፅዮን ከመመራት ተነስቶ በመጨረሻው ደቂቃ ባስቆጠራቸው ጎሎች ሣራ ካኒዛሮን አራት ለሦስት አሸንፏል።

በእንቅስቃሴ ብልጫ እንደመውሰዳቸው ጎል ማስቆጠር ይገባቸው የነበሩት ሣራ ካኒዛሮዎች በጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ በናትናኤል ደበበ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ብልጫ በተወሰደባቸው ቦታዎች ሁሉ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ገና በመጀመርያው አጋማሽ ሦስት ቅያሪዎች ያደረጉት አፍሮ ፅዮኖች ተጨማሪ ጎል ለማስተናገድ የተገደዱ ሲሆን በሣራ ካኒዛሮ በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የተመለከትነው ስዑድ ሽኩር ከአስራ ስድስት ከሀምሳ ውጭ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ የግብጠባቂውን አቋቋም አይቶ በቀጥታ ወደ ጎል በመምታት በግሩም ሁኔታ ለሣራ ካኒዛሮ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

በጨዋታው ተዳክመው የቀረቡት አፍሮ ፅዮኖች የመጀመርያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ በዳዊት ሙሉጌታ አማካኝነት የመጀመርያ ጎላቸውን ማስቆጠር ችለው እረፍት ወጥተዋል። ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ ባስቆጠሩት ጎል ተነቃቅተው ይመጣሉ ቢባልም የሣራ ካኒዛሮው አጥቂ ናትናኤል ደበበ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል በማስቆጠር የቡድኑን የጎል መጠን ወደ ሦስት ማስፋት ችሏል።

ተጨማሪ የተጫዋች ለውጥ ያደረጉት አፍሮ ፅዮኖች ቅያሪያቸው ተሳክቶላቸው ፉአድ ቢንያም የጎል መጡን ማጥበብ የቻሉበትን ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ጥንቃቄ የመረጡት ሣራ ካኒዛሮች ወደ ኃላ ማፈግፈጋቸው ዋጋ አስከፍሏቸው የዳኛው ተጨማሪ ደቂቃ በታየበት ቅፅበት ምትኩ አፍሮ ፅዮንን ሦስት አቻ ማድረግ የሚችል ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ ሲባል በማይታመን ሁኔታ የዳኛው የጨዋታ መጠናቀቅ ፊሽካ ሲጠበቅ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የተጣለለትን ኳስ ወደ ፊት ገፍቶ በመሄድ ፉአድ ቢንያም ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ የማሸነፊያውን አራተኛ ጎል አስቆጥሩ ድራማዊ በሆነ ትዕይንት ጨዋታው ወዲያውኑ ተጠናቋል። በዚህ ውጤት የተደሰቱት አፍረ ፅዮኖች ደስታቸውን በልዩ ሁኔታ ሲገልፁ አስተውለናል።

አፍሮ ፅዮን በዛሬው ዕለት ከመመራት ተነስተው ጣፋጭ ሦስት ነጥብ እንዲያገኙ በመሐል ሜዳ ላይ የቡድኑን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር እና ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል በዛሬው ጨዋታ ልዮነት ፈጣሪ የነበረው አማካይ እና የቡድኑ አንበል ይታገሱ ታሪኩ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ አዳማ ከተማን ከኢትዮጵያ ቡና ያገናኘው የዕለቱ ተጠባቂ ጨዋታ ቡናማዎቹ በጠባብ ውጤት አንድ ለዜሮ አሸናፊነት ተጠናቋል። ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ በቅርቡ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቱ ያለፈው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ቴዎድሮስ አበባውን ለማሰብ ታዳጊዎቹ ባነር ይዘው ወደ ሜዳ በመግባት ያሰቡት ሲሆን በተጨማሪም የህሊና ፀሎት ተደርጎለታል።

ብዙም ማራኪ ያልነበረው እና በጎል ሙከራ ያልታጀበው የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ጎል ቢጠናቀቅም ኢትዮጵያ ቡናዎች መሐል ሜዳውን በመቆጣጠር ረገድ ከአዳማዎች የተሻሉ ነበሩ። ከእረፍት መልስ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ የወሰዱት ቡናዎች በርከት ያሉ የጎል አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ይሁን እንጂ ከቀኝ መስመር ሰብረው የገቡት ቡናዎች ከተሻጋሪ ኳስ ሀምዛ ሱልጠን ብቸኛውን የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል። የቡና ተጫዋቾችም ጎሉን ካስቆጠሩ በኃላ በጋራ በመሆን ቴዎድሮስ አበባው ስም በተዘጋጀው የመታሰቢያ ባነር በመሄድ ደስታቸውን ተንበርክከው እርሱን በመዘከር አስበውታል። ጨዋታውም በዚሁ በኢትዮጵያ ቡና አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ቡናው ዋና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በሜዳ በመገኘት ጨዋታውን የተከታተለ መሆኑ ይህ ለብዙዎች የዋና ቡድን አሰልጣኞች እንደ አስተማሪነቱ የሚወሰድ እና ለታዳጊዎቹ ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር መልካም አጋጣሚ የሚታይ ነው።

የቡድኑ እንቅስቃሴ ጥሩ የነበረ ባይሆንም በግሉ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያደርግ የነበረው የአዳማው የግራ መስመር አጥቂ የሆነው እና ለኢትዮጵያ ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በቅርቡ መጫወት የቻለው ፈቱ ሰፋ ወደ ፊት ተስፋ ከሚጣልባቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆኑን ማሳየት ችሏል።

በማስከተል የአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ የነበረው የፍቅር በአንድነት እና የከለላ ጨዋታ በፍቅር በአንድነት የበላይነት አራት ለዜሮ አሸናፊነት ተጠናቋል። ጎሎቹን በመጀመርያው አጋማሽ መሳይ አሳቦ እና ፍራኦል በቀለ ሲያስቆጥሩ ከእረፍት መልስ ቀሪውን ጎሎች ናትናኤል ግሩም እና አብዱ መሐመድ አስቆጥረው ጨዋታው ተጠናቋል። በፍቅር በአንድነት በኩል አስር ቁጥር ለባሹ እና ሁለተኛውን ጎል በግሩም ሁኔታ ያስቆጠረው ፍራኦል በቀለ በጨዋታው የተመለከትነው ተስፈኛ ታዳጊ ነው።

በሌላ የአዲስ አበባ ስታዲየም አራተኛ ጨዋታ ሀሌታ ከ ጌታቸው ቀጨኔ ያደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ ሲጠናቀቅ ለጌታቸው ቀጨኔ አዲሱ ግርፍ እና ሚኪያስ ታዬ ሲያስቆጥሩ ለሀሌታ ዮርዳኖስ ሞላ እና ሚካኤል ንጉሱ ሁለቱን ጎሎች አስቆጥረዋል።

አቃቂ በሚገኘው መድን ሜዳ በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድን መከላከያን ሦስት ለአንድ ሲያሸንፍ ሳላዲን አብደላ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር የውድድር ዓመቱን ሦስተኛ ጎሉን ሲያስመዘግብ ሌላኛውን ጎል ዮናታን እሸቱ አስቆጥሯል። ለመከላከያ የማስተዛዘኛ ጎል አራፋት ሲራጅ ማስቆጠር ችሏል።

በማስከተል የተካሄደው የቤተል ድሪመርስ እና ኢትዮ ኤሌትሪክ ጨዋታ በኢትዮ ኤሌትሪክ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል። ለኢትዮ ኤሌትሪክ ሁለቱ አሸናፊዎች አሸናፊ መላኩ እና አሸናፊ አበራ ሲያስቆጥሩ የቤተል ድሪምስ ብቸኛ ጎል አማኑኤል ሀጎስ ማስቆጠር ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ