የሁለተኛ ዲቪዚዮን የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ባህር ዳር ከተማን አሸናፊ በማድረግ ተገባዷል

የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች የሁለተኛ ዲቪዚዮን ፕሪምየር ሊግ ባህርዳር ከተማን የዋንጫ አሸናፊ በማድረግ በዛሬው ዕለት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድር ከየካቲት 7 ጀምሮ የሁለተኛው ዙር መርሐ-ግብር በሀዋሳ ከተማ እየተደረገ ቆይቶ ዛሬ ረፋድ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ውድድሩ በይፋ ተጠናቋል፡፡ሊጉም ጠዋት 2 ሰዓት ለገጣፎ ለገዳዲን ከልደታ ክፍለ ከተማ አገናኝቶ ጨዋታው 1ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ በመቀጠል 4፡00 ሲል ባሳለፉነው ሳምንት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን እና የዋንጫ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠው ባህርዳር ከተማ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጋር ተገናኝቶ ቂርቆስ ጨዋታውን 2ለ1 አሸንፏል፡፡ምንም እንኳን በዛሬው ጨዋታ ባህርዳር ከተማዎች ሽንፈት ማስተናገድ ቢችሉም ቀደም ብለው የዋንጫ አሸናፊ መሆናቸውን ማረጋገጥ በመቻላቸው የ2013 የሁለተኛ ዲቪዚዮን ሻምፒዮን የሆኑበትን ዋንጫ ከፍ አድርገዋል።

በመዝጊያው መርሐ-ግብርም የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ፣ የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ፍሬው አራርሳ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ስራ አስፈፃሚ እና የሴቶች ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙ እንዲሁም የፌድሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባላት አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ በክብር እንግድነት በተገኙበት የሽልማት አሠጣጥ እና ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የሰርተፍኬት ስጦታ ተበርክቷል፡፡ በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን በመፈፀሙ የነሀስ ሜዳሊያ ሲሸለም ሁለተኛ በመሆን ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን ያደገው ቦሌ ክፍለ ከተማ የብር ሜዳሊያ ተበርክቶመታል። ወደ አንደኛው ዲቪዚዮን ማደጉን ያረጋገጠው ባህርዳር ከተማ ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ እና አሸናፊ የሆነበትን ዋንጫ ከዕለቱ የክብር እንግዳው ተረክቧል፡፡

በመቀጠል ንግስት በቀለ በ15 ጎሎች የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አግቢ በመሆን ከኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ የዋንጫ ተሸላሚ መሆን የቻለች ሲሆን በቀጣይም በአዲስ አበባ በአንድ ሆቴል በሚደረግ ፕሮግራም ተጨማሪ ሽልማት ይኖራታልም ተብሏል፡፡ ባንቺአየው ደመላሽ በምርጥ ግብ ጠባቂነት፣ ፍቅርተ ታፋ በምርጥ ተጫዋችነት እንዲሁም ሰርክአዲስ ዕውነቱ በምርጥ አሰልጣኝነት ከባህርዳር ከተማ የተመረጡ ሲሆን ስማቸው ይፋ ይሁን እንጂ ከሌሎች የፌዴሬሽኑ ውድድሮች ጋር ሽልማቱ በቀጣይ የሚሰጥ እንደሚሆን ተሰምቷል። በመጨረሻም የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን ለውድድሩ መሳካት የላቀ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላት የሰርተፍኬት ስጦታ ተበርክቶ የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ሁለተኛ ዲቪዚዮን ፕሪምየር ሊግ በይፋ ተጠናቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ