ዋልያዎቹ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ሰርተዋል

በነገው ዕለት ማዳጋስካርን የሚገጥመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ረፋድ የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል።

ካሜሩን ለምታስተናግደው የ2022 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው ዕለት የምድቡ አምስተኛ ጨዋታውን ከማዳጋስካር ጋር ያደርጋል። ብሔራዊ ቡድኑም ከመጋቢት አራት ጀምሮ ጨዋታው በሚደረግበት ባህር ዳር የሦስተኛ ምዕራፍ ዝግጅቱን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን ከቀናት በፊትም ከማላዊ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አከናውኖ ነበር።

ወሳኙን የምድብ ጨዋታ ለማድረግ ዋዜማው ላይ የሚገኘው ቡድኑ ዛሬ ረፋድ ከአራት ሰዓት ጀምሮ ከጨዋታው በፊት ያለውን የመጨረሻ ልምምድ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አከናውኗል። ለአንድ ሰዓት በቆየው ልምምድም ቡድኑን ለነገው ጨዋታ የሚያዘጋጁ ቀለል ያሉ አዝናኝ የሜዳ ላይ የተግባር ሥራዎች ሲሰሩ አስተውለናል። በተጨማሪም ከመስመር የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን ሲከናወኑ ተመልክተናል። ከምንም በላይ ደግሞ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተጫዋቾቹ በሥነ-ልቦናው ረገድ ከፍ እንዲሉ የሚያስችል አነቃቂ ንግግሮችን በሜዳ ላይ ሲያደርጉ አስተውለናል። በንግግሮቹ መሐከልም ተጫዋቾቹ የራሳቸውን አጨዋወት ብቻ ሜዳ ላይ እንዲተገብሩ እና በተጋጣሚ ቡድን የጨዋታ አቀራረብ እንዳይደናገጡ መክረዋል።

ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ እንዳረጋገጠችው ከሆነ ከመናፍ ዐወል ውጪ ሁሉም የቡድኑ አባላት በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ። ከቀናት በፊት ቡድኑን እንደ አዲስ የተቀላቀሉት ወንድሜነህ ደረጄ እና መሳይ ጳውሎስም ከቡድኑ ጋር ልምምድ ሲሰሩ ተመልክተናል።

በተያያዘ ዜና ከነገው ጨዋታ በፊት የሁለቱ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች የቅድመ ጨዋታ አስተያየታቸውን ምሽት ላይ ለጋዜጠኞች እንደሚሰጡ ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ