“ብሔራዊ ቡድናችን በፊፋ የሀገራት ደረጃ ላይ የተሻለ ቦታን እንዲያገኝ ውጤት ማምጣት አለብን” – ዦን ሚሸል ካቫሊ

ከዋልያዎቹ እና ዝሆኖቹ ፍልሚያ ጋር በተመሳሳይ ሰዓት ማዳጋስካርን የሚገጥሙት ኒጀሮች በዋና አሠልጣኛቸው አማካኝነት ሀሳብ ሰጥተዋል።

በ2022 ለሚደረገው የካሜሩን የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የአህጉሪቱ ብሔራዊ ቡድኖች የመጨረሻ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። በምድብ 11 ከኒጀር፣ ኮትዲቯር እና ማዳጋስካር ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚወስደውን ትኬት ለመቁረጥ በዛሬው ዕለት አቢጃን ላይ ወሳኝ ግጥሚያ ከኮትዲቯር ጋር ይጠብቀዋል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ስብስቡ ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለመመለስ ከኮትዲቯር ሦስት ወይም አንድ ነጥብ መውሰድ፤ ያ ካልሆነ ሳይሆን ቀርቶ በኮትዲቯር ከተሸነፈ ደግሞ ኒጀር ማዳጋስካርን የምታሸንፍበትን አልያም ነጥብ የምታስጥልበትን ዕድል ይጠብቃል። በዛሬው ዕለት በተመሳሳይ በምድቡ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የማለፍ ያልተሟጠጠ ዕድል ያላት ማዳጋስካር ኒጀርን በሜዳዋ ትጋብዛለች። ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞም ከምድቡ መውደቋን ቀድማ ያረጋገጠችው ኒጀርን የሚመሩት የ63 ዓመቱ ፈረንሳዊ አሠልጣኝ ዦን ሚሸል ካቫሊ ከጨዋታው በፊት ተከታዩን አጭር ሀሳብ ሰጥተዋል።

“ምንም እንኳን ወደ አፍሪካ ዋንጫው ባናልፍም እያንዳንዱ ጨዋታዎች ወሳኝ ናቸው። በተለይ ብሔራዊ ቡድናችን በካፍ እና ፊፋ የሀገራት ደረጃ ላይ የተሻለ ቦታን እንዲያገኝ ውጤት ማምጣት አለብን። ስለዚህ ዛሬ ከማዳጋስካር ጋር የምናደርገው ጨዋታ ወሳኝ ነው።”

የማዳጋስካር እና የኒጀር ጨዋታ እንደ ኮትዲቯር እና ኢትዮጵያ መርሐ-ግብር በተመሳሳይ 10 ሰዓት እንደሚደረግ ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ