ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል

አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በአሰልጣኝነት ከሾመ ወዲህ ተጠናክሮ ለመቅረብ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

ቡድኑን የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች የሆነው የቀድሞ የባህር ዳር ከተማ አማካይ የነበረው ዳንኤል ኃይሉ ነው። የዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በሰበታ ከተማ መለያ ጀምሮ ከግማሽ ዓመት በኋላ ክለቡን የለቀቀው አማካይ በምስራቅ ኢትዮጵያው ቡድን ለቋሚነት ከዳንኤል ደምሴ እና ሌላው አዲስ ፈራሚ ሄኖክ ገምቴሳ ጋር ፉክክር ይጠብቀዋል።

ሌላው ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋች ያሲን ጀማል ነው። ክለቡ ከተስፋ ቡድን አሳድጎት የነበረው እና በጉዳት ሳቢያ ዘንንሮ ቀንሶት የነበረው ሁለገቡ የመስመር ተከላካይ ያሲን ጀማል ዳግም ወደ ስብስቡ መቀላቀል ችሏል።

በተቃራኒው ቡድኑ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ካስፈረማቸው አማካዩ አስጨናቂ ሉቃስ እና ተከላካዩ ኩዌኩ አንዶህ ጋር መለያየቱ ለማወቅ ተችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ