ዋልያዎቹ አዲስ አበባ ደርሰዋል

ከስምንት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫው መመለሳቸውን ያረጋገጡት ዋልያዎቹ በአሁኑ ሰዓት አዲሰ አበባ ደርሰዋል።

ካሜሩን በ2022 ለምታስተናግደው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ሲያደርጉ የከረሙት ዋልያዎቹ በትላንትናው ዕለት ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚወስዳቸውን ትኬት መቁረጣቸው ይታወሳል። ብሔራዊ ቡድኑም በትላንትናው ዕለት የምድብ የመጨረሻ ጨዋታውን አቢጃን ላይ ከአቮሪኮስት አከናውኖ ነበር። ቡድኑም አዳሩን በአቢጃን ካደረገ በኋላ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ስምንት ሰዓት ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀምሯል። ለአምስት ሰዓት ከሠላሳ ደቂቃ አየር ላይ የቆየው ቡድኑም 2:45 ሲል በቦይንግ 787 አውሮፕላን አዲስ አበባ አርፏል።

ልዑኩ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርስም የባህል እና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶ/ር ሂሩት ካሳ፣ ኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሸን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ እና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተው ለብዱኑ አቀባበል አድርገዋል። የክብር እንግዶቹም ለልዑኩ የአበባ ጉንጉን እና የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ ያረፈበት ስካርቭ አበርክተዋል። በተጨማሪም የክብር እንግዶቹ እና የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የእንኳን ደስ አላችሁ ንግግር አድርገዋል።


በአሁኑ ሰዓትም ልዑኩ ከአየር ማረፊያው የቪአይፒ ክፍል እስኪወጣ በርከት ያሉ የብሔራዊ ቡድኑ ደጋፊዎች እየዘመሩ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ