“አሁን በዚህ ምድር ላይ በጣም ደስተኛው ሰው ነኝ” ኢሳይያስ ጂራ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ስለብሔራዊ ቡድኑ የአቢጃን ቆይታ፣ በጨዋታው ስለተፈጠረው ድራማዊ ክስተት፣ ጨዋታው ሲቋረጥ ለተጫዋቾች ስለገቡት ቃል፣ ስለ ኒጀር ብሔራዊ ቡድን እና ተያያዥ ጉዳዮች የሰጡትን ሀሳብ ይዘን ቀርበናል።

በካሜሩን አዘጋጅነት ለሚካሄደው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ለ16 ወራት የቆየው የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ሲያከናውን የነበረው ዋልያው የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታውን አቢጃን ላይ አከናውኖ በትናንትናው ዕለት አዲስ አበባ ገብቷል። 2:45 ላይ በቦይንግ 787 አውሮፕላን ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የደረሰውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልዑክ እየመሩ የመጡት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ስለ ቡድኑ የአቢጃን ቆይታ፣ በጨዋታው ስለተፈጠረው ድራማዊ ክስተት፣ ጨዋታው ሲቋረጥ ለተጫዋቾች ስለገቡት ቃል፣ ስለ ኒጀር ብሔራዊ ቡድን እና ተያያዥ ጉዳዮች ለተጠየቁት ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው አስፍረነዋል።

የአቢጃን ቆይታ እንዴት ነበር?

“የአቢጃን ቆይታ ጥሩ ነበር። የሀገሪቱ ሙቀት ግን አይቻልም ነበር። ይህ ቢሆንም ግን ውጤቱ ሙቀቱን ሸፍኖታል። የተገኘው ድል በጣም ደስ የሚል ነው። እኔ ግን በስፖርት ቆይታዬ ውስጥ በዚህ ሰዓት (7 ሰዓት) ውድድር ሲደረግ አጋጥሞኝ አያውቅም። ለዛውም 34°C ሙቀት ላይ። ከዚህም አልፎ የውድድሩ የህክምና ተቆጣጣሪ የውሃ እረፍት ከልክሎ ነበር። እንደውም ውድድር ነው ብሎ መናገር አይቻልም፣ እንደ መቀጣጫ አይነት ነገር እንጂ። ቀድመን የጨዋታው ሰዓት እንዲቀየር ለካፍ ጥያቄ ብናቀርብም ከገበያ እና ከቴሌቭዥን መብት ጋር ተያይዞ ቀድሞ ሰዓቱ ስለተወሰነ ማስቀየር አልተቻለም። እንደ እኔ እምነት ግን የማዳጋስካርንም ሆነ የእኛን ጨዋታ ወደ ምሽት መግፋት ይቻል ነበር። ግን አልሆነም። ውጤቱም መታየት የጀመረው ከዳኛው ነው። ዳኛው መንቀሳቀስ ሳይችል በቆመበት ነው የወደቀው። በአጠቃላይ ግን ለሰው ህይወት ከባድ ነበር። ካፍም በቀጣይ ትምህርት መውሰድ አለበት። እርግጥ ካፍ ብቻ ሳይሆን ሌሎቻችንም ከዚህ መማር አለብን። ቅድሚያ ለስፖርተኛው ማሰብ አለብን።”

በፕሬዝደንትነት ዘመንዎ ስላሳኩት ድል?

“አሁን በዚህ ምድር ላይ በጣም ደስተኛው ሰው ነኝ። ተቋሙ ውስጥ መልካም መልካም ነገሮችን ለመስራት እየሞከርን ነው። ነገርግን ይሄ የምንሰራው አስተዳደራዊ ስራዎቻችን በውጤት ካልታጀቡ ፋይዳ የለውም። አሁንም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠብቀውን ነገር ከእኛ አግኝቷል ብዬ አስባለሁ። ከስምንት ዓመታት በኋላም ወደ አፍሪካ ዋንጫው ተመልሰናል። ፈጣሪ ይመስገን እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ።”

ጨዋታው ሲቋረጥ ቡድኑ ላይ ስለነበረው ስሜት እና ለተጫዋቾች ስላስተላለፉት መልዕክት?

“ልክ ጨዋታው ሲቋረጥ እኔ የማዳጋስካርን ጨዋታ እየተከታተለልኝ ወደነበረ ወዳጄ ስልክ ደወልኩ። እንደ አጋጣሚ ሆኖም የመጀመሪያው የድል ብስራት የደረሰው እኔ ጋር ነው። ከዛ ውጤቱን ለቡድኑ ገለፅኩኝ። የቀረውን ዘጠኝ ደቂቃ ለመጨረስ ወደ ሜዳ ከመግባታችን በፊት ደግሞ እኔ ለተጫዋቾቹ ቃል ገብቼ ነበር። ማለፋችንን ብናረጋግጥም የገባብንን ጎል ማጥበብ አለብን በሚል እያንዳንዱ ተጫዋች ጎል ካስቆጠረ ሀምሳ ሀምሳ ሺ ብር እንደምሸልም ገለፅኩ። ግን ይህ አልሆነም። ዋናው ነገር ግን ማለፋችን ነው። በዚህ አጋጣሚ ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምድብ ውስጥ ተደልድሎ ሁሉንም የሜዳ ላይ ጨዋታዎች ያሸነፈው አሁን ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ግን ኒጀር ላሳየችው የስፖርታዊ ጨዋነት ተገዢነት እጅግ በጣም ትልቅ ክብር አለኝ። የምስጋና ደብዳቤም ልኬላቸዋለሁ። በግልም የፌዴሬሽኑን ፕሬዝዳንት አግኝቻቸዋለሁ። እኛ አራት ዕድል ይዘን ነው አቢጃን የሄድነው። ሁለቱ ዕድል አቢጃን ላይ ነበር፣ ሁለቱ ደግሞ ማዳጋስካር ላይ ነበር። ስለዚህ ከአራቱ አንዱ ተሳክቶልናል። በዚህም ፈጣሪ ይመስገን። የኢትዮጵያ ህዝብም እንኳን ደስ አለው ማለት እፈልጋለሁ።”

ፌዴሬሽኑ የአሠልጣኝ ለውጥ አድርጎ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ስለተመለሰበት መንገድ?

“ሁል ጊዜ የምትሰራውን ነገር አምነህ መስራት አለብህ። እገሌ ምን ይለኛል ብለህ አሰራርህን መስበር የለብህም። ፈጣሪ ይመስገን ያስተላለፍነው ውሳኔ ውጤት አፍርቶ ዛሬ ላይ አይተናል። ውሳኔው ልክ ነበር ወይ ብሎ መጠየቅም አያስፈልግም። ማሳያው ይሄ ነው። እኔ ሁል ጊዜ የምለው አንድን ሰው ለመጉዳት ከመስመር አትውጣ፣ አንድን ሰውም ለመጥቀም ከመስመር አትሂድ ነው። ሁሌ በቀናነት ከሰራህ ጊዜ ሊወስድ ይችላል እንጂ ሁሉ ነገር ይሳካል።”

የአፍሪካ ዋንጫው ዝግጅት ምን ሊመስል ይችላል?

“እኔ እንግዲህ የምታወቀው ስራን አከፋፍሎ በመስጠት ነው። አስተዳደራዊ ነገሩን እኔ እሰራለሁ፣ ቴክኒካል ነገሩን ደግሞ ለባለሙያ እሰጣለሁ። መግለፅ የምፈልገው ነገር ግን አስፈላጊውን እገዛ ፌዴሬሽኑ እንደሚያደርግ ነው። ከዚህም አልፎ መንግስት ከእኛ ጎን እንደሚሆን ሙሉ ለሙሉ ተስፋ አደርጋለሁ። በዚህም ችግር አይገጥመንም ብዬ አስባለሁ። እንዳልኩት ግን አስተዳደራዊ በተለይ የፋይናንስ ጉዳዮችን እኛ እናስተካክላለን። በአጠቃላይ ብሔራዊ ቡድኑ መዘጋጀት ባለበት መጠን እና አሠልጣኙ ቡድኑን ማዘጋጀት እፈልጋለሁ በሚልበት መጠን እንዲዘጋጅ ለማገዝ ፌዴሬሽናችን ዝግጁ ነኝ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ