በዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ላይ የተሳተፉ ተጫዋቾች

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጉዞ ላይ ተሳትፎ ያደረጉ ተጫዋቾችን ዝርዝር ከነተጫወቱበት ደቂቃ አሰናድተን ይዘን ቀርበናል።

አንታናናሪቮ ላይ በሽንፈት የተጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች ጉዞ አቢጃን ላይም በሽንፈት ቢገባደድም በቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች በተሰበሰቡ ዘጠኝ ነጥቦች ለ33ኛ ጊዜ ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን አረጋግጧል። ቡድኑ በ16 ወራት ውስጥ ባደረጋቸው ስድስት የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ሠላሳ ሜዳ ገብተው የተጫወቱ ተጫዋቾችን የተጠቀመ ሲሆን እኛም የተጫዋቾቹን የጨዋታ ደቂቃ በማስላት ተከታዩን ዘገባ ይዘን ቀርበናል።

በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ እና ውበቱ አባተ የአሠልጣኝነት ጊዜ ብሔራዊ ቡድኑ ሦስት የግብ ዘቦችን እያፈራረቀ ተጠቅሟል። በዚህም ተክለማርያም ሻንቆ፣ አቤል ማሞ እና ምንተስኖት አሎ በአሠልጣኞቹ የመጫወት ዕድል የተሰጣቸው ግብ ጠባቂዎች ናቸው። ከሦስቱ የግብ ዘቦች ደግሞ በርካታ የመጫወቻ ጊዜን ያገኘው ተጫዋች ተክለማርያም ሻንቆ ነው። ይህ ግብ ጠባቂ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝነት መንበርን አግኝተው ባደረጉት አራቱም ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል። በዚህም ከግብ ጠባቂዎች በርካታ ደቂቃዎችን (360) በማጣሪያ ጨዋታው የተጫወተ ቀዳሚው ተጫዋች ሆኗል። ተጫዋቹም ከተሰለፈባቸው አራት ጨዋታዎች በሁለቱ ግቡን ሳያስደፍር አሳልፏል።

ከተክለማርያም ቀጥሎ በርካታ ደቂቃዎችን የተጫወተው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ ነው። ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን አንታናናሪቮ ላይ ሲያደርግ ሙሉ ደቂቃ የተጫወተው አቤል ባህር ዳር ላይ በተደረገው ሁለተኛው የምድቡ ጨዋታ አርባ አምስት ደቂቃዎችን ተጫውቶ ተቀይሮ መውጣቱ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም ተጫዋቹ አጠቃላይ 135 ደቂቃዎችን ተጫውቷል። ከአቤል በመቀጠል ደግሞ ምንተስኖት አሎ የብሔራዊ ቡድኑን ግብ ለአርባ አምስት ደቂቃዎች ጠብቋል።

ወደ ተከላካዮች ስናመራ ብሔራዊ ቡድኑ ስምንት የተከላካይ መስመር ተጫዋቾችን በስድስቱ የማጣሪያ ጨዋታዎች ወደ ሜዳ አስገብቷል። በትናንትናው ዕለት ባወጣነው ዘገባ መሠረት ስድስቱንም የቡድኑን የማጣሪያ ጨዋታዎች የተሰለፉት ተጫዋቾች አስቻለው ታመነ እና ረመዳን የሱፍ ብቻ ናቸው። 540 ደቂቃዎችን ከተጫወቱት አስቻለው እና ረመዳን በመቀጠል ደግሞ የቡድኑን የኋላ መስመር ለረጅም ደቂቃ የጠበቀው ተጫዋች ያሬድ ባየ ነው። እንደ ተክለማርያም ሁሉ በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ አራት ጨዋታዎች ላይ ሙሉ ተሳትፎን ያደረገው ያሬድ ሁሉንም የጨዋታ ደቂቃዎች (360) ከአስቻለው ታመነ ጋር በመጣመር አሳልፏል።

ቡድኑ ከተጠቀማቸው ሦስት የቀኝ መስመር ተከላካዮች አንዱ የሆነው ሱሌማን ሀሚድ ደግሞ 181 ደቂቃዎችን በማጣሪያ ጨዋታዎቹ አሳልፏል። ከሱሌማን በአንድ ደቂቃ ያነሰ የመጫወቻ ጊዜ ያገኘው አህመድ ረሺድ ደግሞ በአሠልጣኝ አብርሃም ሁለት ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎን አድርጓል። ለመጀመሪያ ጊዜ በመጨረሻው የብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ የተካተተው አሠሥራት ቱንጆ ደግሞ 179 ደቂቃዎች ላይ ተጫውቷል። ከአስቻለው ጋር በመጀመሪያው የቡድኑ ጨዋታ (ከማዳጋስካር ጋር) ተጣምሮ የነበረው አንተነህ ተስፋዬ በበኩሉ በቀጣዩ የአይቮሪኮስት ጨዋታ ተቀይሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በድምሩ 156 ደቂቃዎችን በመጫወት ተከታዩን ደረጃ ይዟል። ባህር ዳር ላይ የተደረገው ጨዋታ ላይ አንተነህ ሲጎዳ ተቀይሮ የገባው ደስታ ደሙ ደግሞ 24 ደቂቃዎች ላይ የአቅሙን ለሀገሩ ሰጥቶ ተጫውቷል።

የአማካይ መስመሩ ላይ ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ አስራ ሦስት ተጫዋቾችን በስድስቱ የማጣሪያ ጨዋታዎች ተጠቅሟል። በሚገርም ሁኔታ ደግሞ የትኛውም ተጫዋች እያንዳንዱን ቡድኑ ያሳለፋቸው ደቂቃዎች ላይ ሙሉ ተሳትፎን አላደረገም። በአንፃራነት ግን ሁሉም ጨዋታዎች ላይ ተሳታፊ የነበረው ሽመልስ በቀለ (ሁለት ጨዋታዎች ላይ ተቀይሮ መውጣቱ ልብ ይሏል) በርካታ ደቂቃዎችን የተጫወተ ቀዳሚው የአማካይ መስመር ተጫዋች ነው። 494 ደቂቃዎች ላይ ለሀገሩ የተጫወተው ሽመልስ ሁለት ጎሎችን ሜዳ ላይ በቆየባቸው ደቂቃዎች ሲያስቆጥር ሁለት ለጎል የሆነ ኳሶችንም ለአጋሮቹ አመቻችቶ አቀብሏል። ከሽመልስ በመቀጠል በርካታ ደቂቃዎችን ለዋልያዎቹ የተጫወተው ተጫዋች ደግሞ ሱራፌል ዳኛቸው ነው። ሱራፌል በተጫወታቸው 345 ደቂቃዎች አንድ ጎል ከመረብ ሲያገናኝ አንድ ወደ ግብነት የተቀየረ ኳስንም አመቻችቶ አቀብሏል።

በሦስተኛ ደረጃ ላይ በርካታ ደቂቃዎችን የተጫወተ የአማካይ ተጫዋች የሆነው ይሁን እንደሻው ነው። ይሁን እንደ ተቀመጠበት ደረጃ ሦስት ጨዋታዎች በአጠቃላይ ደግሞ 181 ደቂቃዎች ላይ የዋልያውን መለያ ለብሶ ተጫውቷል። በመቀጠል ደግሞ አማኑኤል ዮሐንስ በተጫወታቸው 180 ደቂቃዎች ተቀምጧል። አማኑኤል በአብርሃም እና ውበቱ ስር አንድ አንድ የምድቡ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ አራት ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ ያደረገው ሌላኛው ተጫዋች መስዑድ መሐመድ ነው። ከአራቱ ጨዋታዎች ሁለቱ ላይ (የኒጀር የደርሶ መልስ ጨዋታ ላይ) በቋሚነት ወደ ሜዳ የገባው መስዑድ በአጠቃላይ 179 ደቂቃዎችን ተጫውቶ አንድ ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝቷል። እንደ መስዑድ ሁሉ ሀብታሙ ተከስተም በተመሳሳይ 179 ደቂቃዎች ላይ ተሰልፎ የተጫወተ ተጫዋች ነው። ከመሱዑድ እና ሀብታሙ በመቀጠል ደግሞ በሁለት ጨዋታዎች ላይ ሜዳ ላይ ገብቶ የተጫወተው ታፈሰ ሰለሞን በ125 ደቂቃዎች ቀጣዩን ደረጃ ይዟል።

ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመርያ ጨዋታውን ከማዳጋስካር ጋር አከናውኖ አንድ ለምንም ሲሸነፍ ለ62 ደቂቃዎች የተጫወተው ጋቶች ደግሞ ቀጣዩ ቦታ ላይ ተቅጧል። ከጋቶች በመቀጠልም ሽመክት ጉግሳ በ47፣ ሀይደር ሸረፋ በ28፣ ከነዓን ማርክነዕ በ24፣ ጋዲሳ መብራቴ በ7 እንዲሁም ፍፁም ዓለሙ በ2 ደቂቃዎች ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል።

ወደ አጥቂ መስመሩ ጎራ ስንል በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው የቡድኑን የፊት መስመር የመሩት ተጫዋቾች ስድስት ናቸው። ከስድስቱ ተጫዋቾች ደግሞ በርካታ የመጫወቻ ጊዜን ያገኘው አቡበከር ናስር ነው። ከመጀመሪያው የአንታናናሪቮው የማዳጋስካር ጨዋታ ጀምሮ እስከ አቢጃኑ የአይቮሪኮስት ጨዋታ ድረስ በስድስቱም ጨዋታዎች ላይ የተጫወተው አቡበከር በመጀመሪያው እና መጨረሻው ጨዋታ ላይ ተቀይሮ ከመውጣቱ ውጪ ሁሉም ደቂቃዎች ላይ ተጫውቷል። በዚህም ተጫዋቹ ሜዳ ላይ በነበረባቸው 528 ደቂቃዎች አንድ ጎል ሲያስቆጥር አንድ ወደ ጎልነት የተቀየረን ኳስ አመቻቸቶ አቀብሏል። እንደ አቡበከር ሁሉ በስድስቱም ጨዋታዎች የተጫወተው ሌላኛው አጥቂ አማኑኤል ገብረሚካኤል ነው። የመስመር አጥቂው ተቀይሮ የወጣባቸው ጨዋታዎችን ታሳቢ በማድረግ ሜዳ ላይ የተጫወተባቸው ደቂቃዎች ብዛት 393 ነው። ተጫዋቹ በእነዚህ ደቂቃዎች ሁለት ጎሎችን ከመረብ አገናኝቷል።

ከሁለቱ የመስመር አጥቂዎች በመቀጠል የዋልያውን የፊት መስመር ለበርካታ ደቂቃዎች የመራው ተጫዋች ጌታነህ ከበደ ነው። 340 ደቂቃዎችን የተጫወተው የቡድኑ አምበል በአራት ጨዋታዎች ሦስት ጎሎች በስሙ አስመዝግቧል። የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ የሆነው ተጫዋቹ ከመረብ ካገናኛቸው ኳሶች በተጨማሪ አንድ ግብ የሆነ ኳስ አቀብሏል።

አራተኛው በርካታ ደቂቃዎችን የተጫወተው አጥቂ አዲስ ግደይ ነው። በአይቮሪኮስቱ የባህር ዳር ጨዋታ ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ቋሚ ሆኖ ወደ ሜዳ የገባው አዲስ በአጠቃላይ ለ84 ደቂቃዎች ለብሔራዊ ቡድኑ ተጫውቷል። በመቀጠል መስፍን ታፈሰ ለ26 ሙጂብ ቃሲም ደግሞ ለ7 ደቂቃዎች የዋልያውን መለያ ለብሰው የተጫወቱ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ