“በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ኢትዮጵያዊ የሚመስል ቡድን ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን” – ውበቱ አባተ

ዋልያውን ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የመለሱት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ትላንት ምሽት አዲስ አበባ ሲደርሱ ለተነሳላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ ይዘን ቀርበናል።

ለአስራ አንደኛ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ተሳታፊ መሆኑን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንት ምሽት ለአምስት ሰዓት ከሠላሳ የቆየ የአየር ላይ በረራ ካደረገ በኋላ አዲስ አበባ ደርሷል። ቡድኑም ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ ደማቅ አባበል ተደርጎለታል። ከአቀባበሉ በኋላም የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ስለ አቢጃን ቆይታቸው፣ ስለ አይቮሪኮስቱ ጨዋታ፣ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሰለተመለሱበት መንገድ፣ ስለ ኒጀር ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም አጠቃላይ የቡድኑን የማጣሪያ ጉዞ እና አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎን በተመለከተ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ተከታዮቹም ምላሾች ሰጥተዋል።

አቢጃን ስለነበራቸው ቆይታ?

“ከጅምሩ ወደ አፍሪካ ዋንጫው እንገባለን የሚል እቅድ ይዘን ነው የተነሳነው። ፈጣሪም ፍላጎታችንን አሳክቶ ከምድባችን ሁለተኛ ሆነን አልፈናል። ምንም እንኳን በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ በአይቮሪኮስት ሦስት ለአንድ ብንሸነፍም ከመጀመሪያው ጨዋታ ጀምሮ በሰበሰብናቸው ነጥቦች ወደ አፍሪካ ዋንጫው አልፈናል። በዚህም ደግሞ ተደስቻለሁ። ድሉም የመላዊ ኢትዮጵያዊያን ነው። ሁላችንንም ያስደሰተ ነው። በተለይ ደግሞ በዚህ ሰዓት መሆኑ እና የጋራ የሚያደርገውን እግር ኳስ ሲያስደስተን በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል።”

በአይቮሪኮስት ጨዋታ ስለነበረው ከባድ ነገር?

“አንደኛ አይቮሪኮስት ራሱ ከባድ እና ትልቅ ቡድን ነው። እኛ ደግሞ ጨዋታውን ለማሸነፍ በጀብደኝነት ነው ወደ ሜዳ የገባነው። ይህም ደግሞ መጠነኛ ክፍተቶች እንዲፈጠሩብን ያደረገ ይመስለኛል። ትልቅ ትምህርት ግን ከጨዋታው ወስደናል። ወደፊት ባለን ሰፊ ጊዜ ደግሞ እነዚህን ክፍተቶች ለማረም እንሞክራለን። ስለዚህ በቀጣይ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እና በአፍሪካ ዋንጫው የተሻለ ቡድን ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን። በአጠቃላይ የገጠምነው የአፍሪካን ትልቁን ቡድን ነው። ከዚህም መነሻነት ጨዋታው የራሳችንን ብቃት ለማየት እንደ መስታወት ጠቅሞናል።”

ጨዋታው ሲቋረጥ ቡድኑ ላይ ስለነበረው ስሜት እና የኒጀርን ውጤት ስላወቁበት ቅፅበት?

“በጣም ከባድ ነው። የእኛ ጨዋታ እንደተቋረጠ የማዳጋስካር እና የኒጀር ጨዋታ ባዶ ለባዶ እንደሆነ ሰምተናል። ይህም ቢሆን ግን ትኩረታችን ሜዳ ላይ እየተፈጠሩ ባሉት ነገሮች ነበር። በመጨረሻው ደቂቃ ግን የእነሱን ውጤት ነበር ስንከታተል የነበረው።በመጨረሻም ውጤቱን ሲሰሙ ብዙ ተጫዋቾችም ያለቅሱ ነበር። በጣም በውጥረት ላይም እንደነበሩ ያወኩት በዛ ሰዓት ነው። ሰበብ ለማድረግ ሳይሆን ጨዋታው በከፍተኛ ወበቅ የተደረገ ነው። ተጫዋቾቼም እንደፈለጉ መንቀሳቀስ አልቻሉም። ዳኛው ላይም የተፈጠረው ይህ ነው። በአጠቃላይ ግን ደስታው ልዩ ነበር።”

ስለ ቡድኑ ቀጣይ የጨዋታ አቀራረብ?

“አንዳንድ ማሻሻያዎቸን ማድረግ ይጠበቅብናል። ከእያንዳንዱ ቀን እና ነገር ትምህርት ትወስዳለህ። በአይቮሪከኮስቱ ጨዋታ በፍፁም መከላከል የምንጫወትበትን መንገድ ቀይሰን መግባት እንችል ነበር። ከዚህ በላይ ግን መጫወት የምፈልገውን ነገር መሞከራችን ለእኔ ትልቅ ነገር ነው። በሽንፈት ውስጥም ቢሆን ከያዝነው ነገር አለመውጣታችን ለእኔ አስደስቶኛል። ያም ቢሆን ግን ከጨዋታው የተማርናቸው ብዙ ነገሮች ስላሉ ወደፊት የምናስተካክለው ነገር ይኖረናል።”

የአይቮሪኮስቱ ሽንፈት ደስታውን አደብዝዞት ይሆን ?

“በፍፁም! እኛ ከምድቡ የተሻለ ነጥብ ስለሰበሰብን እና የተሻለ ጨዋታ ስላሸነፍን ነው ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፍነው። ዕድሉ የመጣው በሌላ ነው ብለን ግን የተጫዋቾቹን ልፋት ማጣጣል የለብንም። በምድቡ ዘጠኝ ነጥብ አለን። አስር ጎሎችንም ተጋጣሚ ላይ አስቆጥረናል። አራት ንፁ ጎልም አለን። ይሄ ደግሞ በምድብ ማጣሪያ ያልተለመደ ነው። በአይቮሪኮስት ሦስት ጎል ማስተናገድ ለኢትዮጵያ እንግዳ ነው ብሎ ማሰብ ከእግር ኳስ ውጪ ላለው ሰው ነው። እኛ እግር ኳስ ውስጥ ያለን ሰዎች የምናቀው ነው። የዛሬ አመት እኮ በሜዳችን በጅቡቲ ሦስት ጎል ገብቶብናል። ስለዚህ ይሄኛውም ሽንፈት ያን ያህል ከባድ ነው ብዬ ማሰብ አልፈለግም። የእኛ ቡድን አይቮሪኮስትን እዚህ አሸንፏል። በአጠቃላይ ይሄ እግር ኳስ ነው። የሚመጣውን ነገር መቀበል አለብን። ቀና ብለን እንድንሄድ የሚያመለክት ውጤተም ነው ያየነው። በቡድኔ ውስጥም በርካታ ወጣት ተጫዋቾች አሉ። በእነሱም በጣም ነው የኮራሁባቸው።”

ስለ ኒጀር ብሔራዊ ቡድን?

“ኒጀርም ሆነ አይቮሪኮስት ተመሳሳይ ነገር ነው ያደረጉት። ምናልባት አይቮሪኮስት አሸንፋ ኒጀር ብትሸነፍ ማዳጋስካር ታልፍ ነበር። ስለዚህ እነሱ ፕሮፌሽናል ናቸው። ሥራቸውንም ነው የሰሩት። እርግጥ በእነሱ አቻ መውጣት እኛ ያገኘነው ነገር አለ። ግን ይሄ እግር ኳስ ነው። እግር ኳስም የሚሰብከው በፍትሃዊነት መጫወት እንዳለብህ ነው። እነሱም የተገበሩተ ይሄንኑ ነው። በደንብ ፕሮፌሽናል ናቸው። ግን እኛ ኒጀርን ስናሸንፍ ብዙም ቦታ አልተሰጠንም ነበር። ኒጀር ደካማ ነች ነበር የተባለው። ኒጀር ከማዳጋስካር አቻ ወጥታ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ስናልፍ ደግሞ ዋጋውን ለእነሱ የምንሰጥ ከሆነ ጤነኝነት አይደለም። ስለዚህ ሥራቸውን ነው የሰሩት። በዚህም ደግሞ እናመሰግናቸዋለን።”

ከአፍሪካ ዋንጫው ምን እንጠብቅ?

“እኔ ሁልጊዜም የተሻለ ነገር ማድረግ ነው ፍላጎቴ። በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ኢትዮጵያዊ የሚመስል ቡድን ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን። በዚህ ሰዓት ግን ከእግር ኳሳዊው ውጤት በላይ የሚያስደስተኝ ነገር ቡድናችን ውስጥ ያለው ስብጥር በአንድነት ሰርቶ ውጤት ማምጣቱ ነው። ቡድኑ ውስጥ ሙስሊም፣ ኦርቶዶክስ፣ ፕሮቴስታንት እንዲሁም ከተለያየ አካባቢ የመጡ ተጫዋቾች አሉ። በተጨማሪም ለቡድኑ አዲስ የሆኑ እንዲሁም ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች አሉ። ይህ ደግሞ ትክክለኛ የኢትዮጵያ መገለጫ ነው። ስለዚህ ለእኔ ከማሸነፉም በላይ እነዚህ ተጫዋቾች አንድ ሆነው ለሀገር ያሳዩት የአንድነት መንፈስ ነው የሚያስደስተኝ። በዚህም ነገር ደግሞ ኮርቻለሁ። በመጨረሻም ሀገራችንን ሠላም ያድርግልን። ወደፊት ደግሞ የተሻሉ ተጫዋቾችን እናያለን ብዬ አስባለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ