የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዋልያዎቹ የማበረታቻ ሽልማት አበረከተ

ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የተመለሱት ዋልያዎቹ ዛሬ ረፋድ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ሰጪ ኃላኒ አቶ ዣንጥራር ዓባይ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በዛሬ ማለዳ መርሐ ግብር ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና የሥራ ከስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ የዋልያዎቹ የልዑካን ቡድን የተገኘ ሲሆን ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ባለፈችበት ዕለት በንፁሀን ላይ በተፈፀመው ግድያ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የሕሊና ፀሎት ተደርጎ መርሐ ግብሩ ተጀምሯል። በመቀጠልም የከተማው ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የእንኳን ደስ አላችሁ ንግግራቸውን አሰምተዋል።

“የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን በአንድነት ሆኖ ላስመዘገበው ውጤት እጅግ የላቀ ክብር እና አድናቆት ያለው መሆኑን ልገልፅላችሁ እፈልጋለሁ። እኔም ትልቅ ክብር ይሰማኛል። እንኳን ደስ አለን እንኳን ደስ አላችሁ። የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ መሆናችሁን ተከትሎ ዛሬ እጅግ ለሀገራችን የሚያስፈልጋትን የአንድነት ስሜት እንዲነሳሳ አድርጋችኋልና ደግመን ደጋግመን ላስመዘገባችሁት ውጤት ልናከብራችሁ እንወዳለን።

“ይህንን በአንድነት፣ በአብሮነት እና በመተባበር የተገኘውን ታላቅ ደስታ ሳናጣጥም እኩይ እቅዳቸውን በመፈፀም የንፁሃንን ህይወት በመቅጠፍ ሀዘን የጨመሩብንን ክፉዎች ስናስብ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው ብለን አዝነናል። ነገር ግን ከእናነተ በመማር ተስፋ ባለመቁረጥ፣ በአብሮነት እና በአንድነት ሆነን ከሰራን ይሄንንም ምዕራፍ እንደምናሸንፈው አይተናል። ወጣትነት እድሜ ታሪክ ሰርቶ ማለፍን በምኞት የሚያደርጉት ሳይሆን ይልቁንም በትጋት በመስራት የሚጎናፀፉት ክብር ነውና በጥረታችሁ ታሪክ ስላስመዘገባችሁ እና ለዚህም በመብቃታችሁ እንዲሁም ለሀገራችሁ ከእግር ኳስ ውጤት ያለፈ የተለየ የመነቃቃት ስሜት መፍጠር ችላችኋል። ከስምንት ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ካሜሩን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ እንድትሆን ላስቻላችሁ እና የታሪኩ አካል ለሆናችሁ ሁሉ በድጋሜ በራሴ እና በከተማ አስተዳደሩ ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። እንኳን ደስ ያላችሁ።

“በእግር ኳስ በግል የሚመዘገብ ውጤት የለም። ውጤት የሚመጣው ሜዳ ላይ በሚጫወቱት ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆን በአመራሮቹ፣ በአሠልጣኞቹ፣ በተጠባባቂዎቹ፣ በወጌሻዎቹ፣ በባለሙያዎች፣ በአማካሪዎች፣ በደጋፊዎች እና አጠቃላይ ሁሉም በአንድነት ተባብረው እንደ አንድ ሰው ሆነው በሚሰሩት ስራ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ለጀመርነው የብልጽግና እና የመደመር ጎዳና ታላቅ ማሳያ ምሳሌ ነውና ይህንን አጋጣሚ በማጉላታችሁ እጅግ አድርገን እናከብራችኋለን።

“የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ያሳየው የደስታ ስሜት ሁላችንም ጋር ተፈጥሯል። በመላው ኢትዮጵያ ተመሳሳይ የደስታ ማዕበል መጉረፍ የሚያስደስተውን ያህል ሃላፊነቱ ከባድ መሆኑንም ማሰብ ተገቢ ነው። በጅምሩ የድል ጉዞውን አደባባይ ወጥቶ ደስታውን በክብር የገለፀው ህዝብ አደራው ከባድ ነው። አደራውን ለመወጣት ከቀደመው የተሻለ ታሪክ ለማስመዝገብ ሩቅ አስባችሁ በመትጋት አላማችሁ እንድታሳኩ ልባዊ ምኞታችንን እየገለፅን ከጎናችሁ እንደምንቆምም መግለፅ እወዳለሁ።

“አሁን ዋናውን ጉዞ ጀምራችኋል። ጀግኖች ናችሁ። ከፊታችሁ ዓለም ሁሉ የሚያየው ውድድር አለና ኢትዮጵያን በአምባሳደርነት በዓለም አደባባይ ይዛችሁ ትቀርባላችሁ። በካሜሩን ሠላማዊ መድረክ ኢትዮጵያ እንደ ደማቅ ብርሃን እንደምትድቅ በእናንተ ላይ ተስፋ አለን። የአዲስ አበባ አስተዳደርም ይህንን ዓላማችሁን ታሳኩ ዘንድ ከጎናችሁ መሆኑን ለመግለፅ ዛሬ እዚህ ለእናንተ ክብር ለመስጠት እና ለማበረታታት የ5.6 ሚሊየን ብር ስጦታ እና ማበረታቻ በመስጠት አብረናችሁ መቆማችንን እናረጋግጣለን።”

ከወ/ሮ አዳነች ንግግር በመቀጠል የብሔራዊ ቡድኑ ልዑክ እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት ከምክትል ከንቲባዋ እጅ ተቀብለዋል። በዚህም መሰረት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የ200 ሺህ ብር ሽልማት ሲበረከትላቸው ለረዳቶቹ አሥራት አባተ፣ አንዋር ያሲን እና ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ እንዲሁም ለቡድን መሪው ባሕሩ ጥላሁን እና ለቴክኒክ ዳይሬክተሩ ቴዎድሮስ ፍራንኮ ለእያንዳንዳቸው የ150 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ለፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ 90 ሺህ፣ ለአሰልጣኝ ስታፍ እና የህክምና ባለሙያዎች 75,000፣ ለሥራ አስፈፃሚዎች 40,000፣ ለተጠባባቂ ተጫዋቾች 100,000፣ ሜዳ ገብተው ለተጫወቱ ደግሞ 150,000 ሺህ ብር በአጠቃላይ ድምር 5.6 ሚልዮን ብር ሽልማት ተበርተክቷል።

ከሽልማት ሥነ-ስርዓቱ በመቀጠል አሰልጣኝ ውበቱ አባተ፣ አምበሉ ጌታነህ ከበደ እና ፕሬዝዳንቱ አቶ ኢሳይያስ ጂራ ከወ/ሮ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ተረክበዋል። አቶ ኢሳይያስም ለተደረገላቸው አቀባበል የከተማ አስተዳደሩን እና ከንቲባዋን አመስግነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ተዘምሮ የዝግጅቱ ፍፃሜ ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ