አምብሮ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ያለውን ውል አድሷል

ያለፉትን ሁለት ዓመታት በተለያዩ እርከን ለሚገኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች ትጥቅ አቅራቢ ሆኖ ሲሰራ የነበረው አምብሮ ከፌዴሬሽኑ ጋር ያለውን ስምምነት ማራዘሙ ታውቋል።

2019 ላይ በተለያየ እርከን ለሚገኙ የወንድ እና ሴት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች የመጫወቻ እንዲሁም የመለማመጃ ትጥቅ ለማቅረብ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር የተስማማው አምብሮ በቀጣይ አራት ዓመታትም ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጋር አብሮ ለመስራት መስማማቱ ተገልፃል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከደቂቃዎች በፊት ባወጣው መግለጫ ላይ ተቋሙ (አምብሮ) የጋራ ተጠቃሚ በሚያደርገው ስምምነት ደስተኛ በመሆኑ ለቀጣይ አራት ዓመታት ለኢትዮጵያ ወንዶች እና ሴቶች ዋናውና ታዳጊ ብሔራዊ ቡድኖች የመጫወቻ፣ በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ የሚለበስ የልምምድ መለያ እንዲሁም የቴክኒክ እና አመራር ክፍሉ የሚለብሰውን የስፖርት ትጥቅ ለማቅረብ መስማማቱን ገልጿል። ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘው መረጃ መሠረት ደግሞ ሁለቱ ተቋማት ከ24 ወራት በፊት ሲፈራረሙ ለአራት ዓመታት የነበረ ሲሆን ነገርግን በውላቸው ውስጥ ከሁለት ዓመታት በኋላ እንደሁኔታው መራዘም የሚችል አልያም የሚፈርስ አንቀፅ ተካቶ ነበር። በዚህም መሠረት ሁለቱም አካላት ለተጨማሪ አራት ዓመታት አብሮ ለመስራት ተስማምተዋል። በስምምነቱ ከተካተቱ አዳዲስ ጉዳዮች አንዱ ፌዴሬሽኑ የደጋፊዎችን መለየ የማቅረብ መብት እንዲኖረው ማስቻል እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።

በዓለም ላይ ከ150 በላይ ለሚሆኑ ቡድኖች ትጥቅ የሚያቀርበው የእንግሊዙ ትጥቅ አምራች ተቋም አምብሮ በአፍሪካም ከ9 ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች እና ከ34 ፕሮፌሽናል ክለቦች ጋር እንደሚሰራ ይታወቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ