ዕውነታ | የአፍሪካ ዋንጫ መስራቾቹ ከረጅም ዓመታት በኋላ በአንድ መድረክ…

የአፍሪካ ዋንጫ መስራች የነበሩት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ ከረጅም ዓመታት በኋላ በካሜሩኑ አፍሪካ ዋንጫ ላይ ይገኛሉ።

የአፍሪካ ትልቁ የሀገራት ውድድር የሆነው የአፍሪካ ዋንጫ በ1957 ሀ ብሎ ሲጀመር በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ ተሳታፊነት እንደሆነ ይታወሳል (ደቡብ አፍሪካ ተሳታፊ የነበረች ቢሆንም ስትከተለው በነበረው የአፓርታይድ ስርዓት ከውድድሩ እንድትወገድ ሆኗል)። የአህጉሪቱን ውድድር የመሠረቱት እነኚህ ሀገራት ከ1957 ጀምሮ ለአምስት (1957፣ 1959፣ 1963፣ 1970፣ 1976)ጊዜያት አብረው በመድረኩ የተሳተፉ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ በውድድሩ የጋራ ተሳትፎ የነበራቸው ደግሞ በ1976 ነው።

በሀገራችን ኢትዮጵያ ተዘጋጅቶ ሞሮኮን ቻምፒዮን ባደረገው የ1976 ውድድር ላይ ሦስቱ ሀገራት ሲሳተፉ ኢትዮጵያ እና ግብፅ አንድ ምድብ ነበሩ። በወቅቱም ኢትዮጵያ በጊኒ እና ግብፅ ተበልጣ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ከምድብ ተሰናብታ ነበር። በሌላኛው ምድብ የነበረችው ሱዳንም እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ከውድድሩ መሰናበቷ ይታወሳል። በአንፃሩ በውድድሩ ረዘም ያለ ርቀት የተጓዘችው ግብፅ በናይጄሪያ እስከተረታችበት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ድረስ በውድድሩ ተሳትፎ ነበራት። በሚገርም ሁኔታም ሦስቱ የውድድሩ መስራች ሀገራት ከዚህ ውድድር በኋላ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ለተጠጋ ጊዜ ያክል በመድረኩ ሳይገናኙ ቆይተዋል። ይሁንና በ2022 ለሚደረገው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን ያረጋገጡት ሦስቱ ሀገራት ከ46 ዓመታት በኋላ ካሜሩን ላይ ዳግም እንደሚገኙ ተረጋግጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ