ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

በነገ ምሽቱ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ሀዋሳ ከተማ እንደመጀመሪያው ዙር ሁሉ ከኢትዮጵያ ቡና ድል በኋላ ተነቃቅቶ ተከታታይ ስኬት ለማስመዝገብ ጅማ አባ ጅፋር በበኩሉ በሊጉ የመቆየት ተስፋው እንዳይመነምን የነገ ምሽቱን ውጤት አጥብቀው ይፈልጋሉ።

ሀዋሳ ከተማ በ17ኛው ሳምንት ያሳካው ድል ከነጥቡ በተጨማሪ ጨዋታውን ያደረገበት መንገድ ለነገ ፍልሚያውም የሥነ ልቦና ጥንካሬን የሚደርብለት ነው። ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር የታረቀው ቡድኑ ሙሉ ጨዋታውን በትኩረት መጫወት መቻሉን በተለየም ግቡን ሳያስደፍር የመውጣቱን ጠንካራ ጎን ማስቀጠል ይኖርበታል። በጨዋታው ወሳኝ ተጫዋቾቹ መስፍን ታፈሰ እና ኤፍሬም አሻሞን ሳያካትት ለድል መብቃቱ በራሱ ተስፋ የሚሰጠው ሲሆን የወጣት ተጫዋቾቹ ትጋትም በጥሩ ጎኑ ይነሳል። ያም ቢሆን እንደነገው ፍልሚያ ባለ ጨዋታ ሀሳቡን በማጥቃትም ላይ ሲያደርግ እንደመጀመሪያው ዙር የጅማ ጨዋታ ሁሉ ክፍተቶችን መፍጠር እና ግብ ካስተናገደ በኋላም ለማገገም ረጅም ጊዜ ሊፈጅበት ስለሚችል የነገውም ጨዋታ ቀላል ይሆንለታል ማለት አይቻልም።

በእንቅስቃሴ ደረጃ መሻሻል የሚታይበት ጅማ አባ ጅፋር አሁንም ወደ ውጤታማነት መምጣት ቀላል አልሆነለትም። የአሌክስ አሙዙ ፣ ዋለልኝ ገብሬ እና ራሁም ኦስማኑ በአሰላለፉ መካተት በድሬዳዋው ጨዋታ የተሻለ የማጥቃት ጉልበት እና ከወትሮው አንፃር መረጋጋት የታየበት የኋላ ክፍልን እንዲያሳየን ቢያደርግም ሙሉእ መሆን ግን አልቻለም። ከበላዩ ያለው ሲዳማ ከአንድ ጨዋታ ውጤት በላይ በሆነ ርቀት ላይ መቀመጡ ደግሞ ጅማ ነገ ይበልጥ ውጤት የማግኘት ጫና ውስጥ ሆኖ ወደ ሜዳ እንዲገባ ያደርገዋል። በመሆኑም ለስህተት ቦታ የማይሰጥ ቀድሞ ግብ የሚያስቆጥር እና ውጤቱን አስጠብቆ የሚዘልቅ አይነት ቡድን ከአባ ጅፋር ይጠበቃል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አምስት ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱን ሀዋሳ ሲያሸንፍ አንዱን ጅማ ድል አድርጎ የዘንድሮዎን ጨምሮ በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ሀዋሳ 6 ፣ ጅማ 5 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ