ሪፖርት | ፋሲል ከነማ በተፈተነበት ጨዋታ ድል አስመዝግቧል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት መሪው ፋሲል ከነማ በመጨረሻ ደቂቃዎች በተቆጠረ ጎል ሲዳማ ቡናን 2-1 ማሸነፍ ችሏል።

ሲዳማ ቡና ወልቂጤ ከተማን ከረታበት አሰላለፍ ሰንደይ ሙቱኩን ከቅጣት መልስ በአማኑኤል እንዳለ፣ ዮናስ ገረመውን በያሬድ ከበደ ምትክ በማሰለፍ ጨዋታውን ይጀምራል። አሰልጣኝ ሥዩም ከበደን ከኮቪድ መልስ ያገኘው ፋሲል ከነማ በኩል ደግሞ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በበረከት ደስታ ቦታ ተክቶ ለጨዋታው ቀርቧል።

በዘነበው ዝናብ ምክንያት ሜዳው አስቸጋሪ ቢሆንም ጥሩ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ፋሲል ከነማዎች መሪ የሆኑበትን ጎል ያስቆጠሩት ገና በሦስተኛው ደቂቃ ነበር። ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ በተከላካዮች ሲመለስ ሽመክት አግኝቶ አመችቶለት ሙጂብ ቃሲም አስቆጥሯል።

ከጎሉ በኋላ ባሉት አስር ደቂቃዎች ፋሲሎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ወደፊት መጓዝ ሲችሉ በስምንተኛው ደቂቃ በዛብህ ከሳጥን ውጪ መትቶ በፌርኖሌ የተያዘበት ሙከራ የሚጠቀስ ነበር።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ እንቅስቃሴ መግባት የቻሉት ሲዳማዎች በቀሪው የአጋማሹ ደቂቃዎች ብልጫ በማሳየት የጎል ሙከራዎችንም ማድረግ ችለዋል። በ21ኛ ደቂቃ ከቅጣት ምት ሲዲቤ መትቶ ሳማኬ ያወጣበት፣ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ኦኪኪ ሲያሻማ ሳማኬ በአግባቡ ኳሱን ባለማራቁ ዳዊት ተፈራ አግኝቶ ያልተጠቀመበት፣ በ 37ኛው ደቂቃ ብርሀኑ አሻሞ ከርቀት መትቶ ሳማኬ ያወጣበት እንዲሁም 41ኛው ደቂቃ ላይ ማማዱ ሲዲቤ ከግራ መስመር አክርሮ መትቶ ሳማኬ የመለሰበት የሲዳማ ቡናን ብልጫ የሚያሳዩ የጎል እድሎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ በቶሎ ጎል የማስቆጠሩ ተራ የሲዳማ ቡና ሆኗል። በ47ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ሲዲቤ በቀጥታ መትቶ ሳማኬ ሲመልሰው ኳሱን ያገኘው ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ጎልነት ቀይሮት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከጎሉ በኋላ ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ ቀጥሎ 65ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡና በእጅጉ ለጎል ያቃረበውን ሙከሬ አድርጓል። ሀብታሙ ከያሬድ ጋር ታግሎ ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል አመቻችቶ ወደ ጎል የመታው ኳስ ለጥቂት በሚያስቆጭ ሁኔታ ወጥቶበታል።

የመጨረሻዎቹ 15 ደቁቃዎችን ተጭነው የተጫወቱት ፋሲል ከነማዎች የጠራ የጎል ሙከራ ለማድረግ ቢቸገሩም በረከት ደስታ ከእንየው የተነሳውን ኳስ ሞክሮ ፌርኖሌ ሲያድንበት ሰንዴይ ደርሶ ከጎል አካባቢ ባፀዳዎ ኳስ ለግብ ለመቅረብ ሞክረዋል። ፋሲል ደቂቃው እየገፋ በሄደ ቁጥር ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለው የማታ ማታ ድል ያሳኩበትን ጎልም አግኝተዋል። በ86ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው አክርሮ የመታውን ኳስ ፌርኖሌ ሲያድንበት የተሰጠውን የማዕዘን ምት ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ ዓለሙ በአስደናቂ ሁኔታ ዘሎ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ፋሲልን አሸናፊ አድርጓል።


© ሶከር ኢትዮጵያ