የድሬዳዋ የምርመራ ውጤት አሁንም ማወዛገቡን ቀጥሏል

በኮቪድ ምክንያት አስራ ስምንት ዳኞች ተይዘዋል በማለት በተሰጠው ውጤት የተጠራጠሩት ዳኞች ሀረማያ ዩኒቨርስቲ ሲሄዱ ውጤቱ ሌላ ሆኖ መገኘቱ አነጋጋሪ ሆኗል።

የድሬዳዋው ውድድር ሊጠናቀቅ የሁለት ሳምንት ጨዋታዎች በቀሩበት በአሁኑ ወቅት ከሦስት ቀናት በፊት ጨዋታውን ከሚመሩት ዳኞች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በኮሮና መያዛቸው መገለፁ ይታወቃል። ይህ ያስደነገጣቸው አወዳዳሪው አካል እና ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ውጤቱ በመጠራጠር ኮቪድ ተገኘባቸው የተባሉት 18 ዳኞችን በመያዝ በሀረማያ ዩኒቨርስቲ ለድጋሚ ምርመራ መሄዳቸውን መዘገባችን ይታወቃል።

በዛሬው ዕለት በመጣ ውጤት መሠረት ከ18ቱ ውስጥ አስራ ሰባቱ ነፃ ናችሁ በማለት ተነግሯቸዋል። ይህ የውጤት መዛባት ያበሳጫቸው ከጨዋታ የራቁት ዳኞች ያሳለፉት ቀናቶች በጣም ከባድ እንደነበረ እና በስነ ልቦናው መጎዳታቸውን ተናግረዋል። “ሙያችንን በኃላፊነት መንፈስ የምንሰራ ሆነን ሳለ የድሬዳዋው የምርመራ ማዕከል የሌለብን አለባቸው በማለት የተሳሳተ ውጤት በመግለፁ ቅሬታ ፈጥሮብናል።” ብለዋል።

በአስራ ስምንተኛ ሳምንት ሰበታ ከተማ ከጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ አንስቶ ዛሬ እስከተካሄዱት ጨዋታ ድረስ በተለይ በዋና ዳኝነታቸው የምናቃቸው ዳኞች ረዳት በመሆን ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወቃል። ዛሬ የተሰማው መልካም ዜና በቀሪው ሁለት ሳምንት ጨዋታዎች ሁሉም ዳኞች በየምድብ ቦታቸው ያለ ተደራራቢ ጫና ያጫውታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ገና ከጅማሬው አንስቶ እያወዛገበ የሚገኘው የድሬዳዋው የኮሮና ምርመራ ውጤት በብዙዎች ዘንድ ቅሬታ እየፈጠረ መፍትሄ ሳያገኝ እስከ መቼ እንደሚዘልቅ አስገራሚ ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ