ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

ለተጋጣሚዎቹ ወሳኝ የሆነው የነገ ከሰዓቱን ጨዋታ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

በሊጉ በፍጥነት ወደ ድል መመለስ ከሚጠበቅባቸው ቡድኖች መካከል ሁለቱ በዚህ ጨዋታ ይገናኛሉ። በቀጣዩ ሳምንት አራፊ የሚሆኑት ወልቂጤ ከተማዎች ሦስት ሽንፈት ያስተናገዱባት ድሬዳዋን በድል መሰናበት ካልቻሉ መጥፎ ትዝታ ለማትረፍ ተቃርበዋል። ከዕረፍት የተመለሱት አዳማ ከተማዎች ደግሞ ከዚህም በባሰ ሁኔታ ውስጥ ናቸው። በሊጉ ግርጌ የተቀመጡት አዳማዎች አሸናፊ ከሆኑ ስምንት ጨዋታዎች አልፈዋል። የነገው ፍልሚያም ወልቂጤ ወደ አደጋ እየቀረበ ያለበትን ሁኔታ በመግታት ወደ ሀዋሳ ለማምራት አዳማም የተመናመነ ያለው ተስፋውን ለማቅናት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። ከውጤቱ ተፈላጊነት ባሻገር የተጋጣሚዎቹ ደካማ ጎኖች መመሳሰል ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር እና ግቦችን ሊያሳየን እንደሚችል እንድንገምት ያደርገናል።

ወልቂጤ እንደ ቡድን ጥሩ እየተገነባ የመጣበትን መንገድ የሚያስረሱ ደካማ የጨዋታ ቀናት እየገጠሙት ቀስ በቀስ ከሰንጠረዡ አጋማሽ እየተንሸራተተ ወደ አስጊው ዞን ለመምጣት ተገዷል። በግል ስህተቶች እንዲሁም በመከላከል ወቅት በሚታዩ የትኩረት ችግሮች ግቦችን የሚያስተናግደው ቡድኑ ወደ ጨዋታ ለመመለስ በሚያዳርገው ተጋድሎ በርካታ ደቂቃዎችን ለማሳለፍ ሲታገል ይታያል። ቀድሞ መሪ መሆን ከቻል ስድስት ያለፉት ወልቂጤ ከኋላ ያለው ድክመቱ ብቻ ሳይሆን ፊት መስመር ላይ የሚታይበት የአጨራረስ ችግርም እንዲሁ ከውጤት አርቆታል ማለት ይቻላል።

በነገው ጨዋታ ወልቂጤ ከምንም በፊት ራሱን ከግብ ጋር ማስታረቅ ይኖርበታል። ድሬ ላይ አንድም ግብ ያልተሳካለት ቡድኑ እየቀያየረ እየተጠቀመባቸው ካሉት አጥቁዎቹ አንዳቸው ይህን ደካማ ሪከርድ ማስቆም የግድ ይላቸዋል። ከሀዲያ ሀሳዕናው ያልተለመደ የተገደበ የመስመር በተለይ ደግሞ የመስመር የማጥቃት ድፍረት የተሻለ የማጥቃት ሂደትም ነገ ከሠራተኞቹ ይጠበቃል። በዚህ ረገድ ምንአልባትም ከሊጉ ደካማ የመከላከል ሪከርድ ባለቤት ከሆነ ቡድን ጋር መገናኘቱ ለወልቂጤ መልካም አጋጣሚ ሊሆንለት ይችላል። በዛው ልክ ግን ራሱን ቀድሞ ግብ ከማስተናገድ ማዳን እና ሙሉ ለሙሉ ከስህተት መታደግ ሌላኛው ፈተናው ነው።

የረፈደ የቡድን ግንባታ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ የተጋራበት ጨዋታ የመሻሻል ፍንጭ ሰጥቶታል ቢባልም በፈለገው ደረጃ ላይ ደርሷል ለማለት አያስደፍርም። የቡድኑን አከርካሪ በአዲስ ተጫዋቾች ማዋቀሩ ለዚህ መሻሻሉ መነሻ ነው ማለት ሲቻል አንድ የጨዋታ ሳምንት አርፎ መምጣቱ የቡድን ውህደቱ ላይ መሻሻልን እንዲያሳይ ሊረዳው እንደሚችል ይጠበቃል። ነገር ግን እንደተጋጣሚው ሁሉ ከኋላ እና ከፊት ያሉበትን የትኩረት እና የአጨራረስ ችግር መቅረፍም ዋናው ትኩረቱ የሚሆን ይመስላል።

አዳማ ከተማ ከሦስቱ የመጫወቻ ቦታዎች አማካይ ክፍሉ ለግብ የሚሆኑ የመጨረሻ ኳሶችን በማድረሱ በኩል ጥሩ ምልክት እየሰጠ ነው። ይህ ጠንካራ ጎኑን ነገም ማስቀጠል እና አጥቁዎቹን ወደ አግቢነት መመለስ የቡድኑ የጨዋታ ዕቅድ ዋና አላማ መሆኑ አይቀርም። ያም ቢሆን የቁጥር መጠኑን ቢያሳንስም በየጨዋታው ግብ ማስተናገዳቸው ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑ ወልቂጤዎች እንዳይስቆጥሩ መከላከል ለአዳማ ቀላል የቤት ሥራ ነው ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ቡድኑ ዘንድሮ መረቡን ሳያስደፍር መውጣት የቻለው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– የመጀመሪያው የቡድኖቹ የእርስ በእርስ ግንኙነት በወልቂጤ ከተማ 1-0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ