የአሠልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባጅፋር 0-0 ባህር ዳር ከተማ

ለ ጎል ከተገባደደው ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ተቀብሏል።

ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባጅፋር

ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ?
ዛሬ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ ነበርን። በቀላሉ ጎል የሚገባብን ቡድን አልነበርንም። ግን የምናገኛቸው አጋጣሚዎች የሚያስቆጩ ነበሩ። በሁለቱም ጨዋታዎች ላይ ኳሱን ስናጣም ሆነ ስናገኝ በጥሩ ሁኔታ ስንጫወት ነበር። ግን ማሸነፍ የምንችልባቸውን ኳሶች እያገኘን አልተጠቀምንም። ስለዚህ ያለመጠቀም ችግር ነው እንጂ የጎል አጋጣሚዎችን እያገኘን ነው ያለነው።
ስለ ኦስማኦ እና ዋውንጎ  ብቃት?

ተጫዋቾቹን ያስመጣነው ባለን ክፍተት ነው። አሁንም ግን ተጫዋቾቹ ከቡድኑ ጋር ለመዋሀድ ብዙ ይቀራቸዋል። ከስድስት ያልበለጠ ጨዋታ ነው ያደረጉት። አጥቂዎች ሁል ጊዜ ከአማካዮች ጋር ብዙ መናበብ አለባቸው። አጋጣሚ ሆኖ ተጫዋቾቹን በውድድር ዓመት አጋማሽ ነው ያገኘናቸው። እንደዛም ሆኖ ግን በኳስ የሚሰሩት ስራ ጥሩ ነው። አሁን ማበረታታት እና ተጨማሪ ዕድሎችን መስጠት ለአጥቂዎች ጥሩ ነው። 

ከዚህ በኋላ የቡድኑ ትኩረት ምንድን ነው?

የጥሎ ማለፍ ይካሄዳል የሚለው ላይ እኔ እርግጠኛ አደለሁም። በክለባችን በኩል የደረሰኝ ምንም መልዕክት የለም። መተዳደሪያ ደንቡ ምን ይላል የሚለው የክለቡ ጉዳይ ይሆናል። በተረፈ ግን እኔ ለክለቡ ሥነ-ልቦና እና ለተጫዋቾቻችን ቀጥይ እጣ ፈንታ ጥሩ ብቃት ለማሳየት እንሞክራለን። እንዳልኩት ግን ጥሎ ማለፍ ይኑር አይኑር እኔ የማውቀው ነገር የለኝም። እኔ እና ቡድኔ ግን ለሁለቱ ቀሪ ጨዋታዎች እንዘጋጃለን።

ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ

ቡድኑ የፈጠራቸውን የግብ ማግባት ዕድሎችን ስላለመጠቀሙ?

ሁለት አይነት ነገር ነው። አንዳንዱ ከሂደቱ ጋር ተያይዞ ነው። አንዳንዱ ደግሞ በግልፅ ሳጥን ውስጥ የተገኘን ኳስ ነው መጨረስ ያልቻልነው። ተጫዋቾቻችን ጨዋታውን ለማሸነፍ ጫና እና ጉጉት ውስጥ ነበሩ። ከዚህም መነሻነት የምንፈልገውን አላገኘንም።

በመጨረሻዎቹ የሊጉ ጨዋታዎች ነጥቦችን ስለመጣላቸው?

ለሁለተኝነት በምናደርገው ጉዞ ድሬዳዋ ላይ መሸነፍ ከጀመርን ጀምሮ ተጫዋቾቻችን በትልቅ ጫና ውስጥ ናቸው። ያንንም ለማስተካከል በአምሮም ሆነ በአካል ሞክረን ነበር። ግን እስካሁን ጨዋታዎችን ማሸነፍ አልቻልንም።  ወይም ደግሞ ወርቃማ የሚባሉ ዕድሎችን አበላሽተናል።

ሀሪሰንን ተክቶ ወደ ሜዳ ስለገባው ፅዮን ብቃት?

ከፅዮን መሻሻል ጋር ተያይዞ ለሁለቱም ግብ ጠባቂዎችን ዕድል ለመስጠት እየሞከርኩ ነው። ፅዮን ከባለፈው ዓመት በጣም ተሻሽሎ ቀርቧል። ይሄንን ስሜት መጠበቅ እና አቅሙን ከፍ ለማድረግ ነው የሞከርነው።