ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

የነገውን ሁለተኛ ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንዲህ አንስተናል።

ቻምፒዮኖቹ ከአንድ የጨዋታ ሳምንት ዕረፍት በኋላ ወደ ሜዳ ሲመለሱ ላለመውረድ እየተፋለመ ከሚገኘው ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ይገናኛሉ። የጨዋታው ትርጉም ግን ከፋሲል ይልቅ ለድሬዳዋ ከፍ ያለ ነው። በዋናነት የቅርብ ተፎካካሪዎቹ የሆኑት ሲዳማ ቡና እና ወልቂጤ ከተማ ዛሬ በየፊናቸው ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት በማጠናቀቃቸው ድሬዳዋ ነገ ሦስት ነጥቦችን ማሳካት ከቻለ በሊጉ የመቆየት ዕድሉን በእጅጉ ያሰፋል።

ዐፄዎቹ ወደ ዕረፍት ከማምራታቸው በፊት ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ለተመለከተ ውድድሩ ከድል መንገድ ሳይዛነፉ ለመጨረስ ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው መረዳት አይከብድም። የውድድሩ አሸናፊ መሆናቸውን እንደማረጋገጣቸው መጠንም ከዚህ በኋላ ፍልሚያቸው ከሪከርዶች ጋር ይሆናል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ቡድኑ እስካሁን ያልተጠቀመባቸውን እንዲሁም ወጣት ተጫዋቾቹንም ዕድል እየሰጠ ይገኛል። በነገውም ጨዋታ በተመሳሳይ መልኩ ሁል ጊዜም ከመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የማይጠፉ የተወሰኑ ተጫዋቾች አርፈው ልንመለከት እንችላለን። በአጨዋወት ረገድ ግን ቡድኑ ሁሌም እንደሚያደርገው ከግብ ክልሉ ራቅ ብሎ የሚከላከል እና በሚያገኘው ክፍተት ሁሉ ውደ ፊት ገፍቶ ለመጫወት የሚጥር እንደሚሆን ይጠበቃል። በእርግጥ በዚህ ሂደት ውስጥ ውጤቱን አብዝቶ የሚፈልገውን ተጋጣሚውን የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች እንዳይፈጠሩለት ማድረግ ከአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ተጫዋቾች ይጠበቃል።

የዛሬዎቹ ጨዋታዎች ውጤት የድሬዳዋ ከተማን የነገ ጫና ቀነስ ያደረጉት ይመስላሉ። ያም ቢሆን ቡድኑ ማሸነፍን በምንም ሊተካው የማይችል ዓላማው ነው። በብርቱካናማዎች ያለመውረድ ትግል ውስጥ አሁን አሁን እንደቡድን እየታየበት ያለው ጠንካራ ጎን የተነሳሽነት መንፈሱ ነው። በእንደዚህ ዓይነት ወቅቶች በዚህ መጠን የቡድን መንፈስ ከፍ ማለቱ በራሱ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ይረዳል። ከወልቂጤ ጋር በተደረገው የመጨረሻ ጨዋታም ያለ በቂ የማጥቃት እንቅስቃሴ ድል እንዲያስመዘግቡ ያላቸው ተነሳሽነት ያገዛቸው ይመስላል። ነገም ከከባድ ተጋጣሚያቸው ጋር ሲገናኙ የሰሞኑ የማሸነፍ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት አብሯቸው ሊኖር የግድ ይላል። ከዚህ ውጪ የሪችሜንድ ኦዶንጎ ወደ ግብ አስቆጣሪነት መምጣት ለአሰልጣኝ ዘማርያም አንድ ተስፋ የሚሰጥ ጉዳይ ነው። የበረከት ሳሙኤል እና ፍሬዘር ካሳ ጥምረት እየጎለበተ መምጣትም የፋሲል ከነማን ጥቃቶች ለመቋቋም እንደሚያግዛቸው ይገመታል። ከአጨዋወት ምርጫ አንፃር ግን ድሬዎች ነገ ወደ ጥንቃቄ ባመዘነ እና ከኳስ ጋር ፈጣን መልሶ ማጥቃትን ምርጫው ያደረገ አጨዋወት ይዘው እንደሚገቡ ይገመታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በሊጉ እስካሁን ሰባት ጊዜ ተገናኝተዋል። ፋሲል ከነማ ሦስት ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ሲሆን አንድ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ አሸንፏል። በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

– በተገናኙባቸው 6 የሊግ ጨዋታዎች ስምንት ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ፋሲል ከነማ ስድስት ፤ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ሁለት ጎሎች አስቆጥረዋል።