ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው አሳወቁ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ከሦስቱ የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ጋር ባደረገው ውይይት ክለቦቹ በቀጣዩ የውድድር ዘመን የመሳተፍ ፍላጎታቸውን እንደገለፁ አስታውቋል።

ፌዴሬሽኑ ይፋ ያደረገው መረጃ ይህንን ይመስላል:-

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከ3ቱም የትግራይ ክልል የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ጋር ስለ ቀጣይ የውድድር ዘመን ተሳትፏቸው በተመለከተ ውይይት አደረገ።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ አባል እና የማርኬቲንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ ገላጋይ እና የኢ.እ.ፌ ዋና ጸሀፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን የተገኙ ሲሆን የመቐለ 70 እንደርታ፣ የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ ፣ የትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የትግራይ ክልል ስፖርት ኮሚሽን አመራሮች በአካል በመገኘት በተጨማሪም የስሁል ሽረ አመራሮች በአካል መገኘት ባለመቻላቸው በቀጥታ የቴሌ ኮንፍረንስ በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።

በውይይቱ በርካታ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን ክለቦቹ በአሁን ወቅት ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ ያስረዱ ሲሆን አሁን ክለቦቹ ወደ ውድድር ለመመለስ ፍላጎት ቢኖራቸውም ፋይናንስ ትልቅ ማነቆ እንደሚሆንባቸው አስረድተዋል።

ከውይይቱ ያገኟቸውን የሀሳብ ግብዓቶች በመውሰድ ወደ ክለቦቻቸው በመመለስ፣ ከደጋፊዎቻቸው ፣ ከክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር ጋር በመነጋገር በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኒያቸውን እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን በኩል ላደረገው 300,000.00( ሶስት መቶ ሺህ ብር) ድጋፍ፣ እንዲሁም በቅርቡ ላደረገው የተጨማሪ የ300,00.00( ሶስት መቶ ሺህ ብር) ድጋፍ በአጠቃላይ ለተደረገው የ600,000.00(ስድስት መቶ ሺህ) ብር ድጋፍ የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምስጋናውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ክለቦቹ ወደ ውድድር እንዲመለሱ ለማድረግ በሚችለው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።